ዘዳግም 26:6-12 NASV

6 ግብፃውያን ግን ከባድ ሥራ በማሠራት አንገላቱን፤ አሠቃዩንም።

7 ከዚያ በኋላ የአባቶቻችን አምላክ (ያህዌ) ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጮኽን፤ እግዚአብሔርም ጩኸታችንን ሰማ፤ ጒስቊልናችንን፣ ድካማችንንና የተፈጸመብንን ግፍ ተመለከተ።

8 ከዚህ የተነሣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ፣ በታላቅ ድንጋጤ፣ በታምራዊ ምልክትና በድንቅ ከግብፅ አወጣን።

9 ወደዚህ ስፍራ አመጣን፤ ማርና ወተት የምታፈሰውን ይህችን ምድር ሰጠን፤

10 አሁንም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ “እነሆ፣ አንተ የሰጠኸኝን የምድሪቱን በኵራት አምጥቻለሁ።” ቅርጫቱንም በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት አስቀምጠው፤ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ስገድ።

11 ከዚያም አንተ፣ ሌዋዊውና በመካከልህ የሚኖረው መጻተኛ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለአንተና ለቤትህ በሰጠው በጎ ነገር ሁሉ ደስ ይበላችሁ።

12 የዐሥራት ዓመት የሆነውን የሦስተኛውን ዓመት ምርት አንድ ዐሥረኛ ለይተህ ካወጣህ በኋላ በየከተሞችህ ውስጥ በልተው እንዲጠግቡ፣ ለሌዋዊው፣ ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ስጣቸው፤