ዘዳግም 28:54-60 NASV

54 ሌላው ይቅርና በመካከልህ በጣም ደግና ርኅሩኅ የሆነው ሰው እንኳ ለገዛ ወንድሙ ወይም ለሚወዳት ሚስቱ ወይም ለተረፉት ልጆቹ አይራራላቸውም።

55 ከሚበላው ከልጆቹ ሥጋ ላይም ቅንጣት ታህል እንኳ ከእነርሱ ለአንዱ አያቀምስም፤ ከተሞችህ ሁሉ በመከበባቸው ጠላቶችህ ከሚያደርሱብህ ሥቃይ የተነሣ ለእርሱ የቀረለት ይህ ብቻ ነውና።

56 በመካከልህ ተለሳልሳና ተቀማጥላ የምትኖር፣ ከልስላሴና ከቅምጥልነት የተነሣ፣ እግሯን ዐፈር ነክቶት የማያውቅ ሴት፣ የምትወደውን ባሏን፣ የገዛ ወንድ ወይም ሴት ልጆቿን ትንቃለች።

57 ከማሕፀኗ የወጣውን እንግዴ ልጇንና የምትወልዳቸውን ሕፃናት ትጠየፋለች፤ ይህን የምታደርገውም በመከራው ወቅት ጠላቶችህ ከተሞችህን ከበው በሚያስጨንቁህ ጊዜ፣ እነርሱን ደብቃ ለመብላት ስትል ነው።

58 በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የዚህን ሕግ ቃሎች በጥንቃቄ ባትከተልና አስደናቂና አስፈሪ የሆነውን የአምላክህንየእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ስም ባታከብር፣

59 እግዚአብሔር (ያህዌ) አስፈሪ መቅሠፍት፣ አስጨናቂና ለብዙ ጊዜ የሚቈይ መዓት፣ አሠቃቂና በቀላሉ የማይወገድ ደዌ በአንተና በዘሮችህ ላይ ይልክባችኋል።

60 የምትፈራቸውንም የግብፅ በሽታዎች ሁሉ ያመጣብሃል፤ በአንተም ላይ ይጣበቃሉ።