ዘዳግም 3:10-16 NASV

10 በከፍታው ቦታ ላይ የሚገኙትን ከተሞች በሙሉ፣ ገለዓድን እንዳለ፣ እስከ ሰልካና እስከ ኤድራይ ያለውን ባሳንን ሁሉ እንዲሁም በባሳን ውስጥ የሚገኙትን የዐግ ግዛት ከተሞች በእጃችን አደረግን።

11 ከራፋይማውያን ወገን የተረፈ የባሳን ንጉሥ ዐግ ብቻ ነበር። ዐልጋው ከብረት የተሠራ ቁመቱም ዘጠኝ ክንድ፣ ስፋቱ ደግሞ አራት ክንድ ነበር። ይህም እስካሁን በአሞናውያን ከተማ በረባት ይገኛል።

12 በዚያን ጊዜ ከያዝነው ምድር ላይ በአርኖን ሸለቆ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር አንሥቶ በስተ ሰሜን ያለውን ግዛት፣ በተጨማሪም ኰረብታማውን የገለዓድ አገር እኩሌታ ከነከተሞቹ ለሮቤላውያንና ለጋዳውያን ሰጠኋቸው።

13 ቀሪውን የገለዓድ ምድርና የዐግ ግዛት የሆነውን ባሳንን በሙሉ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጠሁ። በባሳን የሚገኘው መላው የአርጎብ ክልል የራፋይማውያን ምድር በመባል ይታወቅ ነበር።

14 ከምናሴ ነገድ የሆነው ኢያዕር፣ እስከ ጌሹራውያንና እስከ ማዕካታውያን ወሰን ድረስ የሚገኘውን መላውን የአርጎብ ምድር ወሰደ፤ ምድሪቱም በስሙ ተጠራች፤ ከዚሁ የተነሣ ባሳን እስከ ዛሬ ድረስ ሓቦት ኢያዕር ትባላለች።

15 ገለዓድንም ለማኪር ሰጠሁት።

16 ነገር ግን የሸለቆውን እኩሌታ ወሰን በማድረግ ከገለዓድ አንሥቶ እስከ አርኖን ሸለቆ፣ ከዚያም የአሞናውያን ድንበር እስከ ሆነው እስከ ያቦቅ ወንዝ ያለውን ግዛት ለሮቤላውያንና ለጋዳውያን ሰጠኋቸው።