ዘዳግም 5:25-31 NASV

25 ከእንግዲህ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ድምፅ ብንሰማ እንሞታለን፤ ይህችም ታላቅ እሳት ፈጽማ ታጠፋናለች፤ ታዲያ ለምን እንሙት?

26 ለመሆኑ ከእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር እኛ እንደ ሰማነው ሁሉ፣ የሕያው እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ድምፅ ሰምቶ በሕይወት ለመኖር የቻለ ከሥጋ ለባሽ ማን አለ?

27 አንተ ቅረብ፤ አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚለውን ሁሉ አዳምጥ፤ ከዚያም አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚነግርህን ሁሉ ንገረን፤ እኛም እንሰማለን፤ እናደርገዋለንም።”

28 ይህን ስትነግሩኝ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰማ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) አለኝ፤ “ይህ ሕዝብ ምን እንዳለህ ሰምቻለሁ፤ ያሉትም ሁሉ መልካም ነው።

29 ታዲያ ለእነርሱም ሆነ ለልጆቻቸው ለዘላለም መልካም እንዲሆንላቸው፣ እኔን እንዲፈሩና ሁል ጊዜ ትእዛዞቼን ሁሉ እንዲጠብቁ እንደዚህ ያለ ልብ ቢኖራቸው ምናለ!

30 ሄደህ ወደየድንኳናቸው እንዲመለሱ ንገራቸው።

31 አንተ ግን እንዲወርሷት በምሰጣቸው ምድር እንዲጠብቋቸው የምታስተምራቸውን ትእዛዞች፣ ሥርዐቶችና ሕጎች ሁሉ እንድሰጥህ እዚሁ ከእኔ ዘንድ ቈይ።”