ዘዳግም 7:5-11 NASV

5 እንግዲህ በእነርሱ ላይ የምታደርጉት ይህ ነው፤ መሠዊያዎቻቸውን አፈራርሱ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶቻቸውን ቊረጡ፤ ጣዖቶቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ።

6 አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቅዱስ ሕዝብ ስለ ሆንህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የራሱ ሕዝብ፣ ርስትም እንድትሆንለት በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ መረጠህ።

7 እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከሌሎች ሕዝቦች በቊጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፤ ቊጥራችሁማ ከሕዝቦች ሁሉ እጅግ አነስተኛ ነበር።

8 ነገር ግን እናንተን በብርቱ እጅ ያወጣችሁ፣ ከባርነት ምድርና ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን መዳፍ የተቤዣችሁ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን ስለወደዳችሁና ለአባቶቻችሁ የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ ነው።

9 ስለዚህም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አምላክ (ኤሎሂም) መሆኑን ዕወቅ፤ እርሱ ለሚወዱትና ትእዛዞቹን ለሚጠብቁት የፍቅሩን ኪዳን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ ታማኝ አምላክ (ኤሎሂም) ነው።

10 ነገር ግን፣ የሚጠሉትን ዐይናቸው እያየ ይበቀላቸዋል፤ የሚጠሉትን ዐይናቸው እያየ ለመበቀል አይዘገይም።

11 ስለዚህ በዛሬው ቀን የምሰጥህን ትእዛዙን፣ ሥርዐቱንና ሕግጋቱን ለመከተል ጥንቃቄ አድርግ።