17 አብርሃምም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ ሣቀና በልቡ፣ “እንዲያው ምንስ ቢሆን የመቶ ዓመት ሽማግሌ የልጅ አባት መሆን ይችላልን? ሣራስ በዘጠና ዓመቷ ልጅ መውለድ ትችላለችን?” አለ።
18 አብርሃም እግዚአብሔርን (ኤሎሂም)፣ “እስማኤልን ብቻ ባርከህ ባኖርህልኝ” አለው።
19 እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) እንዲህ አለ፤ “ይሁን እሺ፤ ነገር ግን ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ፤ እኔም ከእርሱ በኋላ ለዘሩ ሁሉ የሚሆን የዘላለም ኪዳን ከእርሱ ጋር እገባለሁ።
20 ስለ እስማኤልም ቢሆን ልመናህን ሰምቼሃለሁ፤ እርሱንም እባርከዋለሁ፤ ፍሬያማም አደርገዋለሁ፤ እጅግም አበዛዋለሁ፤ የዐሥራ ሁለት አለቆች አባት ይሆናል፤ ታላቅም ሕዝብ አደርገዋለሁ።
21 ኪዳኔን ግን የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ልጅ፣ ከይስሐቅ ጋር አደርጋለሁ።”
22 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከአብርሃም ጋር መነጋገሩን ከፈጸመ በኋላ ወደ ላይ ወጣ።
23 በዚያችም ዕለት አብርሃም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት ልጁን እስማኤልን፣ በቤቱ ውስጥ የተወለዱትንና ከውጭ በገንዘቡ የገዛቸውን ወንዶች በሙሉ ገረዛቸው።