8 እነሆ፤ ወንድ የማያውቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ። እነርሱን ላውጣላችሁና የፈለጋችሁትን አድርጉባቸው። በእነዚህ ሰዎች ላይ ግን አንዳች ነገር አታድርጉባቸው፤ እኔን ብለው ወደ ቤቴ ገብተዋልና።”
9 እነርሱም፣ “ዞር በል! ይህ ሰው ራሱ ትናንት ተሰዶ የመጣ ነው፤ ዛሬ ደግሞ ዳኛ ልሁን ይላል። ዋ! በእነርሱ ካሰብነው የከፋ እንዳና ደርስብህ!” አሉት፤ ከዚያም ሎጥን እየገፈታተሩ የበሩን መዝጊያ ለመስበር ተንደረደሩ።
10 ከቤቱ ውስጥ የነበሩት እንግዶች ግን እጃቸውን በመዘርጋት ስበው ወደ ውስጥ አስገቡት፤ በሩንም ዘጉ።
11 ከዚያም በሩን እንዳያገኙት በቤቱ ደጃፍ ላይ የተሰበሰቡትን ወጣቶችና ሽማግሌዎች ዐይን አሳወሩ።
12 ሁለቱ ሰዎችም ሎጥን እንዲህ አሉት፤ “በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ የአንተ የሆኑ ሰዎች አሉህ? ዐማቾች፣ ወንዶችና ሴቶች ወይም ሌሎች ዘመዶች ካሉህ ቶሎ ብለህ ከዚህ እንዲወጡ አድርግ፤
13 ይህን ስፍራ ልናጠፋው ነው። በሕዝቦቿ ላይ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) የቀረበው ጩኸት ታላቅ በመሆኑ፣ እንድናጠፋት እግዚአብሔር ልኮናል።”
14 ሎጥ ከቤቱ ወጥቶ የሴት ልጆቹ እጮኞች የሆኑትን ዐማቾቹን፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ይህችን ከተማ ሊያጠፋት ነውና በፍጥነት ከዚህ ስፍራ ውጡ” አላቸው፤ ዐማቾቹ ግን የሚቀልድ መሰላቸው።