7 እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።
8 እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) በምሥራቅ፣ በዔድን የአትክልት ስፍራ አዘጋጀ፤ ያበጀውንም ሰው በዚያ አኖረው።
9 እግዚአብሔር አምላክም (ያህዌ ኤሎሂም) ለዐይን የሚያስደስት ለመብልም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በአትክልቱ ቦታ መካከልም የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ እንዲሁም መልካምና ክፉን መለየት የሚያስችለው የዕውቀት ዛፍ ነበረ።
10 የአትክልት ስፍራውን የሚያጠጣ ወንዝ ከዔድን ይፈስ ነበር፤ ከዚያም በአራት ተከፍሎ ይወጣ ነበር።
11 የመጀመሪያው፣ ወርቅ በሚገኝበት በሐዊላ ምድር ዙሪያ ሁሉ የሚፈሰው የፊሶን ወንዝ ነው።
12 ኤውላጥ ምርጥ የሆነ ወርቅ፣ መልካም መዐዛ ያለው ከርቤና የከበረ ድንጋይ የሚገኙበት ምድር ነው።
13 ሁለተኛው፣ በኢትዮጵያ ምድር ዙሪያ ሁሉ የሚፈሰው የግዮን ወንዝ ነው።