ዘፍጥረት 20:9-15 NASV

9 ከዚያም አቢሜሌክ አብርሃምን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ይህ ያደረግህብን ነገር ምንድን ነው? ምን በደልሁህና ነው በእኔና በግዛቴ ላይ እንዲህ ያለውን ታላቅ የጥፋት መዘዝ ያመጣብህን? በእውነቱ መደረግ የማይገባውን ነው ያደረግህብን።”

10 ከዚያም አቢሜሌክ፣ “ለመሆኑ ይህን ያደረግህበት ምክንያት ምንድን ነው?” ሲል አብርሃምን ጠየቀው።

11 አብርሃምም አቢሜሌክን እንዲህ አለው፤ “እዚህ ቦታ ፈሪሀ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አለመኖሩን ተገነዘብሁ፤ ሰዎቹም ለሚስቴ ሲሉ ይገድሉኛል ብዬ ሠጋሁ፤

12 ደግሞም እኮ በእርግጥ እኅቴ ናት፤ ከአንድ እናት ባንወለድም በአባት አንድ ነን፤ ኋላም አገባኋት።

13 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አዞኝ ከአባቴ ቤት ወጥቼ በየአገሩ ስዞር፣ ‘ለእኔ ያለሽን ፍቅር በዚህ ግለጭልኝ፤ በየደረስንበት ስፍራ ሁሉ “እርሱ ወንድሜ ነው” በዪ’ ብያት ነበር።”

14 ከዚያም አቢሜሌክ፣ በጎችና የቀንድ ከብቶች፣ ወንድና ሴት አገልጋዮችን ለአብርሃም ሰጠው፤ ሚስቱን ሣራንም መለሰለት።

15 አቢሜሌክም አብርሃምን፣ “እነሆ፤ አገሬ አገርህ ናት፤ በፈቀድህበት ስፍራ መኖር ትችላለህ” አለው።