ዘፍጥረት 24:5-11 NASV

5 አገልጋዩም፣ “ሴቲቱ ከእኔ ጋር ወደዚህ ምድር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆን ምን አደርጋለሁ? ልጅህን አንተ ወደ መጣህበት አገር ልውሰደውን?” ሲል ጠየቀው።

6 አብርሃምም እንዲህ አለው፤ “ምንም ቢሆን ልጄን ወደዚያ እንዳትመልሰው ተጠንቀቅ፤

7 ከአባቴ ቤት፣ ከትውልድ አገሬ ያወጣኝና፣ ‘ለዘርህ ይህችን ምድር እሰጣለሁ’ ብሎ በመሐላ ተስፋ የገባልኝ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መልአኩን ከፊትህ ይልካል፤ ለልጄም ሚስት ከዚያ ታመጣለታለህ።

8 ሴቲቱ አብራህ ወደዚህ ለመምጣት ፈቃደኛ ካልሆነች ግን ካስማልሁህ መሐላ ነጻ ትሆናለህ፤ ነገር ግን ወደዚያ አትውሰደው” አለው።

9 ስለዚህም አገልጋዩ እጁን ከጌታው ከአብርሃም ጭን በታች አድርጐ ስለዚህ ጒዳይ ማለለት።

10 አገልጋዩም ከጌታው ግመሎች መካከል ዐሥሩን ወሰደ፤ ምርጥ ምርጡንም ዕቃ ሁሉ ጭኖ፣ የናኮር ከተማ ወደምትገኝበት ወደ ሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ተጓዙ።

11 እዚያም እንደ ደረሰ፣ ግመሎቹን ከከተማው ውጭ የውሃ ጒድጓድ አጠገብ አንበረከከ፤ ጊዜውም ጥላ የበረደበት፣ ሴቶች ውሃ ለመቅዳት የሚወጡበት ነበር።