ዘፍጥረት 3:10-16 NASV

10 አዳምም፣ “ድምፅህን በአትክልቱ ስፍራ ሰማሁ፤ ዕራቍቴን ስለ ሆንሁ ፈራሁ፤ ተሸሸግሁም” ብሎ መለሰ።

11 እግዚአብሔርም፣ (ያህዌ)፣ “ዕራቍትህን መሆንህን ማን ነገረህ? ‘ከእርሱ እንዳትበላ’ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህን?” አለው።

12 አዳምም፣ “ይህች ከእኔ ጋር እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት፣ እርሷ ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” አለ።

13 እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሴቲቱን፣ “ይህ ያደረግሽው ምንድን ነው?” አላት። እርሷም፣ “እባብ አሳሳተኝና በላሁ” አለች።

14 እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) እባብን እንዲህ አለው፤ “ይህን ስለ ሠራህ፣“ከከብቶችና ከዱር እንስሳት ሁሉተለይተህ የተረገምህ ሁን፤በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፣ በደረትህእየተሳብህ ትሄዳለህ፤ዐፈርም ትበላለህ።

15 በአንተና በሴቲቱ፣በዘርህና በዘሯ መካከል፣ጠላትነትን አደርጋለሁ፤እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።”

16 ሴቲቱንም እንዲህ አላት፤“በምጥ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛለሁ፤በሥቃይም ትወልጃለሽ፤ፍላጐትሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፤እርሱም የበላይሽ ይሆናል።”