26 ከዚያም ላባ ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “ምን ማድረግህ ነው? አታልለኸኛል፤ ልጆቼን የጦር ምርኮኛ ይመስል አካልበህ ወሰድሃቸው።
27 ለመሆኑ ለምን ተደብቀህ ሄድህ? ለምንስ አታለልኸኝ? ብትነግረኝ ኖሮ፣ በደስታና በዘፈን በከበሮና በበገና አልሸኝህም ነበር?
28 የልጆቼን ልጆችና ልጆቼንም ስሜ ብሰናበት ምን ነበረበት? የሠራኸው የጅል ሥራ ነው።
29 ልጐዳችሁ እችል ነበር፤ ዳሩ ግን ባለፈው ሌሊት የአባታችሁ አምላክ (ኤሎሂም) ‘ያዕቆብን፣ ክፉም ሆነ ደግ እንዳትናገረው ተጠንቀቅ’ አለኝ።
30 አንተ ወደ አባትህ ቤት ለመመለስ ስለ ናፈቅህ ሄደሃል፤ ነገር ግን የቤቴን የጣዖት ምስል የሰረቅኸው ለምንድ ነው?”
31 ያዕቆብም ለላባ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ሴቶች ልጆችህን በኀይል ነጥቀህ ታስቀርብኛለህ ብዬ ስለ ፈራሁ ነው።
32 ነገር ግን ከእኛ መካከል የአንተን የጣዖታት ምስል ደብቆ የተገኘ ሰው ካለ ይሙት። ያንተ የሆነ አንዳች ነገር ከኔ ዘንድ ቢገኝ፣ አንተው ራስህ ዘመዶቻችን ባሉበት ፈልግና ውሰድ።” ይህን ሲል፣ ራሔል የጣዖታቱን ምስል መስረቋን ያዕቆብ አያውቅም ነበር።