9 ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአባቴ የአብርሃም አምላክ፣ የአባቴ የይስሐቅ አምላክ (ኤሎሂም) ሆይ፤ ‘ወደ አገርህና ወደ ዘመዶችህ ተመለስ፤ እኔም በጎ ነገር አደርግልሃለሁ’ ያልኸኝ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤
10 እኔ ባሪያህ እስካሁን ላደረግህልኝ ቸርነትና ታማኝነት ብቁ አይደለሁም፤ ዮርዳኖስን ስሻገር በእጄ ላይ ከነበረው በትር በስተቀር ምንም አልነበረኝም፤ አሁን ግን ይኸው ሁለት ሰራዊት ሆኛለሁ።
11 ከወንድሜ ከዔሳው እጅ እንድታድነኝ እለምንሃለሁ፤ መጥቶ እኔንም ሆነ እነዚህን እናቶች ከነልጆቻቸው ያጠፋናል ብዬ ፈርቻለሁና፤
12 ነገር ግን፣ አንተ ራስህ፣ ‘አበለጽግሃለሁ፤ ዘርህንም ሊቈጠር እንደማይቻል እንደ ባሕር አሸዋ አበዛዋለሁ’ ብለኸኛል።”
13 በዚያችም ሌሊት ያዕቆብ እዚያው አደረ፤ ካለው ሀብት ለወንድሙ ለዔሳው እጅ መንሻ እነዚህን መረጠ፦
14 ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችና ሃያ አውራ ፍየሎች፣ ሁለት መቶ እንስት በጎችና ሃያ አውራ በጎች፣
15 ሠላሳ የሚያጠቡ ግመሎች ከነግልገሎቻቸው፣ አርባ ላሞችና ዐሥር ኮርማዎች፣ ሃያ እንስት አህዮችና ዐሥር ተባት አህዮች።