10 እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “ምንድ ነው ያደረግኸው? ስማ! የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል።
11 እንግዲህ የተረገምህ ነህ፤ የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፏን ከከፈተችው መሬት ትሰደዳለህ።
12 ብታርሳትም ፍሬዋን አትለግስህም፤ በምድር ላይ ኰብላይና ተንከራታች ትሆናለህ።”
13 ቃየንም እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ “ቅጣቴ ልሸከመው ከምችለው በላይ ነው።
14 እነሆ፤ ዛሬ ከምድሪቱ አባረርኸኝ፤ ከፊትህም እሸሸጋለሁ፤ በምድር ላይ ኰብላይና ተንከራታች እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።”
15 እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን፣ “የለም! እንደርሱ አይሆንም፤ ማንም ቃየንን ቢገድል፣ ሰባት ዕጥፍ የበቀል ቅጣት ይቀበላል” አለው፤ ስለዚህ፣ ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው እግዚአብሔር (ያህዌ) በቃየን ላይ ምልክት አደረገለት።
16 ቃየንም ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወጥቶ ሄዶ፣ ከዔድን በስተ ምሥራቅ በምትገኝ ኖድ በተባለች ምድር ተቀመጠ።