16 የእንጀራ ቤት አዛዡም፣ ለመጠጥ አላፊዎቹ አለቃ ሕልም፣ የተሰጠው ፍቺ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ሲሰማ፣ የራሱን ሕልም ለዮሴፍ እንዲህ ሲል ነገረው፤ “እኔም ደግሞ ሕልም አይቻለሁ፤ ሦስት መሶቦች በራሴ ላይ ተሸክሜ ነበር፤
17 በላይኛው መሶብ ውስጥ ለፈርዖን የተዘጋጀ የተለያየ ምግብ ነበረበት፤ ወፎችም ራሴ ላይ ካለው መሶብ ይበሉ ነበር።”
18 ዮሴፍም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “የሕልሙ ፍቺ ይህ ነው፤ ሦስቱ መሶብ ሦስት ቀን ነው፤
19 በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፤ በዕንጨትም ላይ ይሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል።”
20 በሦስተኛውም ቀን የፈርዖን የልደት በዓል ነበረ፤ ለሹማምቱም ሁሉ ግብር አበላ። በዚያኑ ዕለትም የመጠጥ አሳላፊዎችን አለቃና የእንጀራ ቤት አዛዡን ሹማምቱ ካሉበት ከእስር ቤት አወጣቸው።
21 የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃ ወደ ቀድሞ ሹመቱ መለሰው፤ እርሱም እንደ ቀድሞው ጽዋውን ለፈርዖን በእጁ ይሰጠው ጀመር፤
22 የእንጀራ ቤት አዛዡን ግን ልክ ዮሴፍ እንደ ተረጐመላቸው ሰቀለው።