26 ሰባቱ የሚያማምሩ ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፣ ሰባቱም የሚያማምሩ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙም አንድና ተመሳሳይ ነው።
27 ከእነርሱም በኋላ ዐጥንታቸው የወጣ አስከፊ መልክ ያላቸው ሰባት ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፤ እንደዚሁም ፍሬ አልባ የሆኑትና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁት ሰባት የእሸት ዛላዎች ሰባት የራብ ዓመታት ናቸው።
28 “አስቀድሜ ለፈርዖን እንደተናገርኩት፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ ፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን ገልጦለታል።
29 በመላው የግብፅ ምድር እጅግ የተትረፈረፈ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ።
30 ከዚህ በኋላ ግን በተከታታይ ሰባት የራብ ዓመታት ይሆናሉ። የራቡ ዘመን አገሪቱን እጅግ ስለሚጐዳት፣ በግብፅ የነበረው ያለፈው የጥጋብ ዘመን ሁሉ ጨርሶ አይታወስም።
31 ከጥጋቡ ዓመታት በኋላ የሚመጣው የራብ ዘመን እጅግ ጽኑ ከመሆኑ የተነሣ፣ ቀደም ሲል የነበረው የጥጋብ ዘመን ፈጽሞ ይረሳል።
32 ሕልሙ ለፈርዖን በሁለት መልክ በድጋሚ መታየቱ፣ ነገሩ ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ዘንድ የተቈረጠ ስለ ሆነ ነው፤ ይህንንም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በቅርብ ጊዜ ይፈጽመዋል።