ዘፍጥረት 42:28-34 NASV

28 እርሱም ወንድሞቹን፣ “ኧረ ብሬ ተመልሶልኛል፤ ይኸው ስልቻዬ ውስጥ አገኘሁት” አላቸው።ሁሉም ልባቸው በድንጋጤ ተሞልቶ እየተንቀጠቀጡ በመተያየት፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ምን ሊያመጣብን ይሆን?” አሉ።

29 በከነዓን ምድር ወዳለው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ ከደረሱ በኋላ፣ ያጋጠማቸውን ሁሉ እንዲህ ብለው ነገሩት፤

30 “የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው ምድሪቱን እንደምንሰልል ቈጥሮን በቍጣ ተናገረን።

31 እኛ ግን እንዲህ አልነው፤ ‘እኛ የታመንን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አይደለንም።

32 እኛ የአንድ አባት ልጆች የሆን፣ ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን፤ አንዱ የለም፤ ታናሽ ወንድማችን ግን ከአባታችን ጋር በከነዓን ይገኛል።’

33 “ከዚህ በኋላ የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው እንዲህ አለን፤ ‘ታማኝ ሰዎች መሆናችሁን የማውቀው በዚህ ነው፤ ከእናንተ መካከል አንዱን ወንድማችሁን እዚህ እኔ ዘንድ ትታችሁ የተቀራችሁት ለተራቡት ቤተ ሰቦቻችሁ እህል ይዛችሁላቸው ሂዱ።

34 ነገር ግን ታናሽ ወንድማችሁን ወደ እኔ አምጡት። በዚያንም ጊዜ ታማኝ ሰዎች እንጂ ሰላዮች አለመሆናችሁን ዐውቃለሁ፤ ወንድማችሁንም መልሼ እሰጣችኋለሁ፤ እናንተም በምድሪቱ እንደ ልብ ለመዘዋወር ትችላላችሁ።” ’