24 የቤቱ አዛዥ ሰዎቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገብቶ እግራቸውን የሚታጠቡበት ውሃ አቀረበላቸው፤ ለአህዮቻቸውም የሚበሉት ገፈራ ሰጣቸው።
25 ምሳ በዚያ እንደሚበሉ ተነግሯቸው ስለ ነበር፣ ዮሴፍ በቀትር ከመግባቱ በፊት እጅ መንሻዎቻቸውን ለማበርከት ተዘጋጁ።
26 ዮሴፍም ወደ ቤቱ ሲገባ ያመጧቸውን እጅ መንሻዎች አበረከቱለት፤ ወደ መሬት ዝቅ ብለውም እጅ ነሡት።
27 ዮሴፍም ስለ ደኅንነታቸው ጠየቃቸው፤ ከዚያም “ሽማግሌ አባት እንዳላችሁ ነግራችሁኝ ነበር፤ ደኅና ነው? አሁንም በሕይወት አለ?” አላቸው።
28 እነርሱም መልሰው፣ “አገልጋይህ አባታችን አሁንም በሕይወት አለ፤ ደኅና ነው’። በማለት ወደ መሬት ዝቅ ብለው በአክብሮት እጅ ነሡት።
29 ዮሴፍ በዐይኑ ሲቃኝ የእናቱን ልጅ ብንያምን አየና፣ “ያ የነገራችሁኝ ታናሽ ወንድማችሁ ይህ ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። ብንያምንም፣ “ልጄ፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይባርክህ” አለው።
30 ዮሴፍ ወንድሙን በማየቱ ስሜቱ በጥልቅ ስለ ተነካ፣ ፈጥኖ ከፊታቸው ገለል አለ፤ ሰወር ያለ ቦታም ፈልጎ፣ ዕልፍኙ ውስጥ አለቀሰ።