6 እስራኤልም፣ “ሌላ ወንድም አለን ብላችሁ ለዚያ ሰው በመንገር ለምን ይህን ችግር እንዲደርስብኝ አደረጋችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
7 እነርሱም፣ “ሰውየው ስለ ራሳችንና ስለ ቤተ ሰባችን አጥብቆ ጠየቀን፤ እንደ ገናም አባታችሁ አሁንም በሕይወት አለ? ሌላስ ወንድም አላችሁ’ ሲል ጠየቀን። እኛም ለጥያቄው መልስ ሰጠነው። ታድያ፣ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ወደዚህ እንድትመጡ’ እንደሚል እንዴት ማወቅ እንችል ነበር?” ብለው መለሱለት።
8 ይሁዳም አባቱን እስራኤልን እንዲህ አለው “ልጁን ከእኔ ጋር ስደደው፤ እኛም በቶሎ እንሂድ፤ ይህ ከሆነ፣ አንተም፣ እኛም፣ ልጆቻችንም አንሞትም፤ እንተርፋለን።
9 ስለ ልጁ ደኅንነት እኔ ራሴ ኀላፊ ነኝ፤ ስለ እርሱም በግል ተጠያቂ እሆናለሁ፤ እርሱንም በደኅና መልሼ ባላመጣውና እዚህ በፊትህ ባላቆመው ለዘላለም በደለኛ እኔ ልሁን።
10 ይህን ያህል ባንዘገይ ኖሮ፣ እስካሁን ሁለት ጊዜ ደርሰን መመለስ በቻልን ነበር።”
11 ከዚህ በኋላ አባታቸው እስራኤል እንዲህ አላቸው፤ “ነገሩ እንዲህ ከሆነስ ይህን አድርጉ፤ ምድሪቱ ከምታፈራው ምርጥ ነገሮች ጥቂት በለሳን፣ ጥቂት ማር፣ ሽቱ፣ ከርቤ ተምርና ለውዝ በየስልቻችሁ ይዛችሁ ለዚያ ሰው እጅ መንሻ ውሰዱለት።
12 በየስልቾቻችሁ አፍ ላይ የተገኘውን ብር መመለስ ስላለባችሁ፣ ዕጥፍ ገንዘብ ያዙ፤ ያ በየስልቾቻችሁ ውስጥ የተገኘው ብር ምናልባት በስሕተት የመጣ ሊሆን ይችላል።