ዘፍጥረት 45:18-24 NASV

18 ከዚያም አባታችሁንና ቤተ ሰባችሁን ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እጅግ ለም ከሆነው የግብፅ ምድር እሰጣችኋለሁ፤ በምድሪቱ በረከት ደስ ብሎአችሁ ትኖራላችሁ።’

19 “ደግሞም እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፤ ‘ይህን አድርጉ፤ ከግብፅ ምድር ልጆቻችሁንና ሚስቶቻችሁን የምታጓጉዙበት ሠረገላዎች ወስዳችሁ፣ አባታችሁን ይዛችሁት ኑ።

20 ስለ ንብረታችሁ ምንም አታስቡ፣ ከግብፅ ምድር እጅግ ለም የሆነው የእናንተ ይሆናልና።’ ”

21 የእስራኤልም ልጆች ይህንኑ አደረጉ። ዮሴፍም ፈርዖን ባዘዘው መሠረት ሠረገላዎች አቀረበላቸው፤ የመንገድም ስንቅ አስያዛቸው።

22 ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት የክት ልብስ ሰጣቸው፤ ለብንያም ግን ሦስት መቶ ጥሬ ብርና አምስት የክት ልብስ ሰጠው።

23 ለአባቱም በግብፅ ምድር ከሚገኘው የተመረጠ ነገር በዐሥር አህዮች፣ እንደዚሁም ለመንገዱ ስንቅ የሚሆነው እህል፣ ዳቦና ሌላ ምግብ በዐሥር እንስት አህዮች አስጭኖ ሰደደለት።

24 ከዚህ በኋላ ወንድሞቹን አሰናበታቸው፤ ከእርሱም ሲሰናበቱ፣ መንገድ ላይ እንዳትጣሉ” አላቸው።