7 ከዚያም ዮሴፍ አባቱን ለመቅበር ወጣ፤ የፈርዖን ሹማምት በሙሉ፣ የቤተ መንግሥቱ ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖች እንዲሁም የግብፅ ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖች ሁሉ ተከተሉት።
8 እንደዚሁም የዮሴፍ ቤተ ሰዎች፣ ወንድሞቹና ሌሎችም የአባቱ ቤተ ሰዎች በሙሉ አብረውት ሄዱ። በጌሤም የቀሩት ሕፃናት ልጆቻቸው፣ የበግ፣ የፍየልና የከብት መንጋዎቻቸው ብቻ ነበሩ።
9 እንዲሁም ሠረገሎችና ፈረሰኞች አብረውት ወጡ፤ አጀቡም እጅግ ብዙ ነበረ።
10 እነርሱም በዮርዳኖስ ማዶ ካለው አጣድ ከተባለው ዐውድማ ሲደርሱ፣ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ምርር ብለው አለቀሱ፤ ዮሴፍም በዚያ ለአባቱ ሰባት ቀን ልቅሶ ተቀመጠ።
11 በዚያ የሚኖሩ ከነዓናውያን በአጣድ ዐውድማ የተደረገውን ልቅሶ ባዩ ጊዜ፣ “ይህ ለግብፃውያን መራራ ልቅሶአቸው ነው” አሉ። በዮርዳኖስ አጠገብ ያለው የዚያ ቦታ ስም አቤል ምጽራይም ተብሎ መጠራቱም ከዚሁ የተነሣ ነበር።
12 የያዕቆብ ልጆችም አባታቸው እንዳዘዛቸው አደረጉ፤
13 አስከሬኑን ወደ ከነዓን ምድር ወስደው አብርሃም ከኬጢያዊው ከኤፍሮን ላይ ከነዕርሻው በገዛው፣ በመምሬ አጠገብ፣ በማክፌላ ዕርሻ በሚገኘው ዋሻ ውስጥ ቀበሩት።