1 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅንና በመርከቧ ውስጥ ከእርሱ ጋር የነበሩትን የዱርና የቤት እንስሳት ሁሉ አሰበ፤ በምድር ላይ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ ውሃውም ጐደለ።
2 የጥልቁ ምንጮችና የሰማይ ውሃ መስኮቶች ተዘጉ፤ ዝናቡም መዝነቡን አቆመ።
3 ውሃው ከምድር ላይ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጣ፤ ከመቶ አምሳ ቀን በኋላም ጐደለ።
4 በሰባተኛው ወር፣ በዐሥራ ሰባተኛው ቀን መርከቧ በአራራት ተራሮች ላይ ዐረፈች።
5 ውሃው እስከ ዐሥረኛው ወር ድረስ እየቀነሰ መጣ፤ በዐሥረኛው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ጫፎች ታዩ።