20 ከቆጵሮስና ከቀሬና የመጡት አንዳንዶች ሰዎች ግን ወደ አንጾኪያ ሄደው ለግሪኮችም ጭምር በመንገር የጌታን የኢየሱስን ወንጌል ሰበኩላቸው።
21 የጌታም እጅ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ቍጥራቸውም እጅግ ብዙ የሆኑ ሰዎች አምነው ወደ ጌታ ተመለሱ።
22 ወሬውም በኢየሩሳሌም ከነበረችው ቤተ ክርስቲያን ጆሮ ደረሰ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱም በርናባስን ወደ አንጾኪያ ላከችው።
23 እርሱም እዚያ ደርሶ እግዚአብሔር በጸጋው የሠራውን ባየ ጊዜ ደስ አለው፤ ሁሉም በፍጹም ልብ በጌታ በመታመን እንዲጸኑ መከራቸው።
24 እርሱም መንፈስ ቅዱስንና እምነትን የተሞላ ደግ ሰው ነበር፤ ቍጥሩ ብዙ የሆነ ሕዝብም ወደ ጌታ ተጨመረ።
25 ከዚህ በኋላ በርናባስ፣ ሳውልን ለመፈለግ ወደ ጠርሴስ ሄደ፤
26 ባገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ አመጣው። ሁለቱም እዚያ ካለችው ቤተ ክርስቲያን ጋር በመሆን አንድ ዓመት ሙሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም ለመጀመሪያ ጊዜ በአንጾኪያ ‘ክርስቲያን’ ተብለው ተጠሩ።