ሐዋርያት ሥራ 18:23-28 NASV

23 በአንጾኪያም ጥቂት ጊዜ ከቈየ በኋላ፣ ከዚያ ተነሥቶ በገላትያና በፍርግያ አገሮች ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ደቀ መዛሙርትን ሁሉ አበረታታ።

24 በዚህ ጊዜ የእስክንድርያ ተወላጅ የሆነ አጵሎስ የሚባል አንድ አይሁዳዊ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ እርሱም የተማረና ቅዱሳት መጻሕፍትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነበር።

25 ይህ ሰው፣ የጌታን መንገድ የተማረ፣ ስለ ኢየሱስም በትክክል የሚናገርና በመንፈስ እየተቃጠለ የሚያስተምር ነበር፤ ይሁን እንጂ እርሱ የሚያውቀው የዮሐንስን ጥምቀት ብቻ ነበር።

26 እርሱም በምኵራብ በድፍረት ይናገር ጀመር፤ ጵርስቅላና አቂላም በሰሙት ጊዜ፣ ወደ ቤታቸው ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ይበልጥ አስተካክለው አስረዱት።

27 አጵሎስ ወደ አካይያ ለመሄድ በፈለገ ጊዜ፣ ወንድሞች አበረታቱት፤ በዚያ የነበሩት ደቀ መዛሙርትም እንዲቀበሉት ደብዳቤ ጻፉለት። እዚያም በደረሰ ጊዜ ከጸጋው የተነሣ አምነው ለነበሩት ትልቅ ረዳት ሆናቸው፤

28 ከቅዱሳት መጻሕፍት እያመሳከረ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ከአይሁድ ጋር በጽኑ በመከራከር በሕዝብ ፊት ይረታቸው ነበርና።