ሐዋርያት ሥራ 3:9-15 NASV

9 ሕዝቡም ሁሉ እየተራመደና እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ ባዩት ጊዜ፣

10 ይህ ሰው ቀደም ሲል ‘ውብ’ በተባለው የቤተ መቅደስ መግቢያ በር ላይ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረው እርሱ መሆኑን ዐወቁ፤ በእርሱ ላይ ከተፈጸመውም ነገር የተነሣ በመደነቅና በመገረም ተሞሉ።

11 የተፈወሰውም ለማኝ ከጴጥሮስና ዮሐንስ ጋር ጥብቅ ብሎ አብሮአቸው ሳለ፣ ሕዝቡ ሁሉ በመገረም እነርሱ ወደነበሩበት ‘የሰሎሞን መመላለሻ’ ወደተባለው ስፍራ እየሮጡ መጡ።

12 ጴጥሮስም ይህን ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ በዚህ ለምን ትደነቃላችሁ? ደግሞም በእኛ ኀይል ወይም በእኛ ጽድቅ ይህ ሰው ድኖ እንዲመላለስ እንዳደረግነው በመቊጠር፣ ለምን ወደ እኛ አትኵራችሁ ትመለከታላችሁ?

13 የአባቶቻችን አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው፤ እናንተ ግን እንዲሞት አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ጲላጦስ ሊፈታው ቢፈልግም እናንተ በእርሱ ፊት ካዳችሁት፤

14 ቅዱሱንና ጻድቁን ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩ እንዲፈታላችሁ ለመናችሁ፤

15 የሕይወት መገኛ የሆነውን ገደላችሁት፤ እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤ እኛም ለዚህ ምስክሮች ነን።