1 የደቀ መዛሙርት ቍጥር እየጨመረ በሄደበት በዚህ ወቅት፣ ከግሪክ አገር የመጡ አይሁድ በይሁዳ ይኖሩ በነበሩት አይሁድ ላይ አጒረመረሙ፤ ምክንያቱም በየዕለቱ በሚከናወነው ምግብ የማደል አሠራር ላይ ከእነርሱ ወገን የሆኑት መበለቶች ችላ ተብለው ነበር።
2 ስለዚህ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሌሎችን ደቀ መዛሙርት በአንድነት ሰብስበው እንዲህ አሉ፤ “እኛ የማእዱን አገልግሎት ለማስተናገድ ስንል የእግዚአብሔርን ቃል አገልግሎት መተው አይገባንም።
3 ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ ከእናንተ መካከል በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ለመሆናቸው የተመሰከረላቸውን ሰባት ሰዎች ምረጡ፤ ይህን ኀላፊነት ለእነርሱ እንሰጣለን፤
4 እኛ ግን በጸሎትና በቃሉ አገልግሎት እንተጋለን።”
5 አባባሉ ሁላቸውን ደስ አሰኘ፤ በእምነትና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላውን እስጢፋኖስን፣ እንዲሁም ፊልጶስን፣ ጵሮኮሮስን፣ ኒቃሮናን፣ ጢሞናን፣ ጰርሜናንና ወደ ይሁዲነት ገብቶ የነበረውን አንጾኪያዊውን ኒቆላዎስን መረጡ።