8 ከዚህ የተነሣም በከተማዪቱ ታላቅ ደስታ ሆነ።
9 ነገር ግን ከዚህ ቀደም ሲል በከተማዪቱ ውስጥ እየጠነቈለ የሰማርያን ሰዎች ሁሉ ያስገረመ፣ ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ራሱን እንደ ታላቅ ሰው ይቈጥር ነበር።
10 ከታናሽ እስከ ታላቅ ያለው ሰው ሁሉ፣ “ይህ ሰው ‘ታላቁ ኀይል’ በመባል የሚታወቀው መለኮታዊ ኀይል ነው” በማለት ከልብ ያዳምጡት ነበር፤
11 ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በጥንቈላ ሥራው ስላስገረማቸውም ትኵረት ሰጥተው ይከተሉት ነበር።
12 ነገር ግን ፊልጶስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሰበከላቸውን አምነው በመቀበላቸው ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ፤
13 ራሱ ሲሞን እንኳ ሳይቀር አምኖ ተጠመቀ፤ ፊልጶስንም ተከትሎ ሄደ፤ የሚደረገውን ምልክትና ታላቅ ታምራት አይቶም ተገረመ።
14 በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል መቀበላቸውን በሰሙ ጊዜ፣ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ እነርሱ ላኳቸው።