ራእይ 10:2-8 NASV

2 በእጁም የተከፈተች ትንሽ ጥቅልል መጽሐፍ ይዞ ነበር፤ ቀኝ እግሩን በባሕር ላይ፣ ግራ እግሩን በምድር ላይ አኖረ፤

3 እንደሚያገሣ አንበሳም ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮኸ፤ በጮኸም ጊዜ የሰባቱ ነጐድጓዶች ድምፆች ተናገሩ።

4 ሰባቱ ነጐድጓዶች በተናገሩ ጊዜ፣ ለመጻፍ ተዘጋጀሁ፤ ነገር ግን፣ “ሰባቱ ነጐድጓዶች የተናገሩትን በማኅተም ዝጋው እንጂ አትጻፍ” የሚል ድምፅ ከሰማይ ሰማሁ።

5 ከዚህ በኋላ በባሕርና በምድር ላይ ቆሞ ያየሁት መልአክ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ አነሣ፤

6 እርሱም ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚኖረው፣ ሰማይንና በውስጡ ያሉትን፣ ምድርንና በውስጧ ያሉትን፣ ባሕርንና በውስጡ ያሉትን በፈጠረው በእርሱ ማለ፤ እንዲህም አለ፤ “ከእንግዲህ መዘግየት አይኖርም፤

7 ነገር ግን ሰባተኛው መልአክ መለከቱን በሚነፋባቸው ቀኖች፣ ለአገልጋዮቹ ለነቢያት በገለጠላቸው መሠረት የእግዚአብሔር ምስጢር ይፈጸማል።”

8 ከዚያም ከሰማይ የሰማሁት ድምፅ እንደ ገና እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “ሂድ፤ በባሕርና በምድር ላይ ከቆመው መልአክ እጅ የተከፈተችውን ጥቅልል መጽሐፍ ውሰድ።”