ራእይ 15:3-8 NASV

3 የእግዚአብሔር ባሪያ የሆነውን የሙሴን መዝሙርና የበጉን መዝሙር እንዲህ እያሉ ይዘምሩ ነበር፤“ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ ሆይ፤ሥራህ ታላቅና አስደናቂ ነው።የዘመናት ንጉሥ ሆይ፤መንገድህ ጽድቅና እውነት ነው።

4 ጌታ ሆይ፤ አንተን የማይፈራ፣ስምህን የማያከብርስ ማን ነው?አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና።የጽድቅ ሥራህ ስለ ተገለጠ፣ሕዝቦች ሁሉ ይመጣሉ፤በፊትህም ይሰግዳሉ።

5 ከዚህ በኋላም አየሁ፤ በሰማይ ያለው ቤተ መቅደስ፣ ይኸውም የምስክሩ ድንኳን ተከፍቶ ነበር፤

6 ሰባቱን መቅሠፍቶች የያዙት ሰባቱ መላእክት ከቤተ መቅደሱ ወጡ፤ እነርሱም ከተልባ እግር የተሠራ ንጹሕ የሚያበራ ልብስ ለብሰው፣ ደረታቸውንም በወርቅ መታጠቂያ ታጥቀው ነበር።

7 ከዚያም ከአራቱ ሕያዋን ፍጡራን አንዱ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚኖረው አምላክ ቊጣ የተሞሉትን ሰባት የወርቅ ጽዋዎች ለሰባቱ መላእክት ሰጣቸው።

8 ቤተ መቅደሱም ከእግዚአብሔር ክብር፣ ከኀይሉም በወጣው ጢስ ተሞላ፤ የሰባቱ መላእክት ሰባት መቅሠፍቶች እስኪፈጸሙ ድረስ ማንም ወደ ቤተ መቅደሱ መግባት አልቻለም።