ራእይ 16:13-19 NASV

13 ከዚያም ከዘንዶው አፍ፣ ከአውሬው አፍና ከሐሰተኛው ነቢይ አፍ እንቍራሪት የሚመስሉ ሦስት ርኩሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ።

14 እነርሱም ምልክቶች የሚያደርጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸው፤ ሁሉን በሚችል አምላክ ታላቅ ቀን ለሚሆነው ጦርነት እንዲሰበስቧቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይሄዳሉ።

15 “እነሆ፤ እንደ ሌባ እመጣለሁ፤ ዕራቍቱን እንዳይሆን ኀፍረቱም እንዳይታይ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ሰው ብፁዕ ነው።”

16 እነርሱም ነገሥታቱን በዕብራይስጥ አርማጌዶን በሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው።

17 ሰባተኛውም መልአክ ጽዋውን በአየር ላይ አፈሰሰ፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ካለው ዙፋን “ተፈጸመ” የሚል ታላቅ ድምፅ ወጣ።

18 ከዚያም መብረቅ፣ ድምፅ፣ ነጐድጓድና ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ሰው በምድር ላይ ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ የምድር መናወጥ ታይቶ አይታወቅም፤ ነውጡም እጅግ ታላቅ ነበር።

19 ታላቂቱ ከተማ ከሦስት ተከፈለች፤ የሕዝቦች ከተሞችም ፈራረሱ፤ እግዚአብሔርም ታላቂቱን ባቢሎን አስታወሰ፤ በብርቱ ቍጣው ወይን ጠጅ የተሞላውን ጽዋ ሰጣት።