ራእይ 16:8-14 NASV

8 አራተኛውም መልአክ ጽዋውን በፀሓይ ላይ አፈሰሰ፤ ፀሓይም ሰዎችን በእሳት እንድታቃጥል ኀይል ተሰጣት።

9 እነርሱም በታላቅ ሐሩር ተቃጠሉ፤ በእነዚህም መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ እንጂ ንስሓ አልገቡም፤ ክብርም አልሰጡትም።

10 አምስተኛውም መልአክ ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ የአውሬውም መንግሥት በጨለማ ተዋጠ፤ ሰዎችም ከሥቃያቸው የተነሣ ምላሳቸውን ያኝኩ ነበር፤

11 ደግሞም ከሥቃያቸውና ከቊስላቸው የተነሣ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ እንጂ ከሥራቸው ንስሓ አልገቡም።

12 ስድስተኛውም መልአክ ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከምሥራቅ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲዘጋጅላቸው የወንዙ ውሃ ደረቀ።

13 ከዚያም ከዘንዶው አፍ፣ ከአውሬው አፍና ከሐሰተኛው ነቢይ አፍ እንቍራሪት የሚመስሉ ሦስት ርኩሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ።

14 እነርሱም ምልክቶች የሚያደርጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸው፤ ሁሉን በሚችል አምላክ ታላቅ ቀን ለሚሆነው ጦርነት እንዲሰበስቧቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይሄዳሉ።