ራእይ 19:3-9 NASV

3 ደግሞም እንዲህ አሉ፤“ሃሌ ሉያ!ጢስ ከእርሷ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል።”

4 ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችና አራቱ ሕያዋን ፍጡራን በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው አምላክ ወድቀው ሰገዱ፤ እንዲህም አሉ፤“አሜን፣ ሃሌ ሉያ!”

5 ከዚህ በኋላ እንዲህ የሚል ድምፅ ከዙፋኑ ወጣ፤“እናንተ አገልጋዮቹ ሁሉ፣እርሱን የምትፈሩ፣ታናናሾችና ታላላቆችም፣አምላካችንን አመስግኑ!”

6 ደግሞም እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ፣ እንደ ኀይለኛ ወራጅ ውሃ ድምፅ፣ እንደ ብርቱም ነጐድጓድ ድምፅ የሚመስል እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ሃሌ ሉያ!ሁሉን ቻይ ጌታ አምላካችን ነግሦአልና።

7 የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ፣የእርሱም ሙሽራ ራሷን ስላዘጋጀች፣ደስ ይበለን፤ ሐሤት እናድርግክብርም እንስጠው።

8 የሚያንጸባርቅና ንጹሕ፣ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ እንድትለብስ ተሰጣት።”ከተልባ እግር የተሠራው ቀጭን ልብስ የቅዱሳን የጽድቅ ሥራ ነው።

9 መልአኩም፣ “ ‘ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው’ ብለህ ጻፍ” አለኝ፤ ቀጥሎም፣ “እነዚህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃሎች ናቸው” አለኝ።