ራእይ 22:2-8 NASV

2 ወንዙም በከተማዪቱ አውራ መንገድ መካከል ይፈስ ነበር። በወንዙ ግራና ቀኝ በየወሩ እያፈራ ዐሥራ ሁለት ጊዜ ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ የዛፉም ቅጠሎች ሕዝቦች የሚፈወሱባቸው ነበሩ።

3 ከእንግዲህ ወዲህ ርግማን ከቶ አይኖርም፤ የእግዚአብሔርና የበጉ ዙፋን በከተማዪቱ ውስጥ ይሆናል፤ አገልጋዮቹም ያመልኩታል፤

4 ፊቱን ያያሉ፤ ስሙም በግምባራቸው ላይ ይሆናል።

5 ከእንግዲህ ወዲህ ሌሊት አይኖርም፤ ጌታ አምላክ ስለሚያበራላቸው የመብራት ወይም የፀሓይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣሉ።

6 መልአኩም፣ “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኞች ናቸው። የነቢያት መናፍስት ጌታ አምላክ በቅርብ የሚሆነውን ነገር ለአገልጋዮቹ እንዲያሳይ መልአኩን ልኮአል” አለኝ።

7 “እነሆ፤ ቶሎ እመጣለሁ፤ የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።”

8 እነዚህን ነገሮች የሰማሁና ያየሁ እኔ ዮሐንስ ነኝ። እነዚህን ነገሮች በሰማሁና ባየሁ ጊዜ፣ እነዚህን ነገሮች ላሳየኝ መልአክ ልሰግድ በእግሩ ሥር ተደፋሁ፤