ራእይ 3:14-20 NASV

14 “በሎዶቅያ ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ አሜን የሆነው፣ ደግሞም ታማኝና እውነተኛ ምስክር የሆነው፣ የእግዚአብሔርም ፍጥረት ገዥ የሆነው እንዲህ ይላል፤

15 ቀዝቃዛ ወይም ትኵስ እንዳልሆንህ ሥራህን ዐውቃለሁ፤ ቀዝቃዛ ወይም ትኵስ ብትሆን በወደድሁ ነበር።

16 እንግዲህ ለብ ያልህ ብቻ እንጂ ትኵስ ወይም ቀዝቃዛ ስላልሆንህ ከአፌ አውጥቼ ልተፋህ ነው።

17 ‘ሀብታም ነኝ፤ ባለጠጋ ነኝ አንዳችም አያስፈልገኝም’ ትላለህ፤ ነገር ግን ጐስቋላ፣ ምስኪን፣ ድኻ፣ ዕውርና፣ የተራቈትህ መሆንህን አታውቅም።

18 ስለዚህ ሀብታም እንድትሆን፣ በእሳት የነጠረ ወርቅ እንድትገዛ፣ የዕራቍትነትህ ኀፍረት እንዳይታይ፣ ነጭ ልብስ እንድትለብስና ለማየት እንድትችል ዐይንህን በኵል እንድትኳል እመክርሃለሁ።

19 እኔ የምወዳቸውን እገሥጻለሁ፤ እቀጣለሁም። ስለዚህ ትጋ፤ ንስሓም ግባ።

20 እነሆ፤ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ሰምቶ በሩን ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ ገብቼ ከእርሱ ጋር እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።