3 እንግዲህ የተቀበልኸውንና የሰማኸውን አስታውስ፤ ታዘዘውም፤ ንስሓም ግባ። ባትነቃ ግን እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ፤ በየትኛው ሰዓት እንደምመጣብህም አታውቅም።
4 ነገር ግን ልብሳቸውን ያላሳደፉ ጥቂት ሰዎች በሰርዴስ ከአንተ ጋር አሉ፤ እነርሱም ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ፤ ይህ የሚገባቸው ነውና።
5 ድል የሚነሣም እንደ እነርሱ ነጭ ልብስ ይለብሳል፤ እኔም በአባቴና በመላእክቱ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም።
6 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።
7 “በፊላድልፍያ ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው፣ የዳዊትንም መክፈቻ በእጁ የያዘው እንዲህ ይላል፤ እርሱ የከፈተውን ማንም ሊዘጋው አይችልም፤ የዘጋውንም ማንም ሊከፍተው አይችልም።
8 ሥራህን ዐውቃለሁ፤ እነሆ፤ ማንም ሊዘጋው የማይችል የተከፈተ በር በፊትህ አድርጌአለሁ። ኀይልህ ትንሽ እንደሆነ ዐውቃለሁ፤ ሆኖም ቃሌን ጠብቀሃል፤ ስሜንም አልካድህም።
9 እነሆ፣ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉት፣ የሚዋሹት፣ ከሰይጣን ማኅበር የሆኑት ወደ አንተ እንዲመጡ በእግርህ ሥር እንዲሰግዱ፣ እኔ እንደ ወደድሁህም እንዲያውቁ አደርጋለሁ።