11 መጽሐፍ እንደሚለው፣ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም።”
12 በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ልዩነት የለም፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፤ የሚለምኑትንም አብዝቶ ይባርካል፤
13 “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።”
14 ታዲያ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ስለ እርሱስ ሳይሰሙ እንዴት ያምኑበታል? ሰባኪ ሳይኖር እንዴት መስማት ይችላሉ?
15 ካልተላኩስ እንዴት መስበክ ይችላሉ? ይህም፣ “የምሥራችን የሚያመጡ እግሮች እንዴት ያማሩ ናቸው!” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።
16 ነገር ግን የሰሙት ሁሉ የምሥራቹን ቃል አልተቀበሉም፤ ኢሳይያስም፣ “ጌታ ሆይ፤ መልእክታችንን ማን አምኖአል?” ብሎአልና።
17 እንግዲያስ እምነት የሚገኘው መልእክቱን ከመስማት ነው፤ መልእክቱም በክርስቶስ ቃል ነው።