ሮሜ 14 NASV

በወንድምህ ላይ አትፍረድ

1 በእምነቱ ደካማ የሆነውን ሰው፣ አከራካሪ በሆኑ ጒዳዮች ላይ በአቋሙ ሳትፈርዱበት ተቀበሉት።

2 የአንድ ሰው እምነቱ ማንኛውንም ነገር እንዲበላ ይፈቅድለታል፤ በእምነቱ ያልጠነከረው ሌላው ሰው ግን አትክልት ብቻ ይበላል።

3 ማንኛውንም የሚበላ የማይበላውን አይናቅ፤ የማይበላውም፣ የሚበላውን አይኰንን፤ እግዚአብሔር ተቀብሎታልና።

4 ሌላውን በሚያገለግል ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ? እርሱ ቢወድቅ ወይም ቢቆም ለጌታው ነው፤ ጌታ ሊያቆመው ስለሚችልም ይቆማል።

5 አንድ ሰው አንዱን ቀን ከሌላው የተሻለ ቅዱስ አድርጎ ይቈጥራል፤ ሌላው ደግሞ ቀኖች ሁሉ እኩል እንደሆኑ ያስባል። እያንዳንዱ የራሱን ውሳኔ ልብ ብሎ ይወስን።

6 አንድን ቀን ከሌላው የተለየ አድርጎ የሚያስብ ሰው፣ እንዲህ የሚያደርገው ለጌታ ብሎ ነው፤ ሥጋ የሚበላውም ለጌታ ብሎ ይበላል፤ ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀርባልና። የማይበላም ለጌታ ሲል አይበላም፤ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ያቀርባል።

7 ከእኛ ማንም ለራሱ የሚኖር፣ ለራሱም የሚሞት የለምና።

8 ብንኖር ለጌታ እንኖራለን፤ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን፤ ስለዚህ ብንኖርም ብንሞትም የጌታ ነን።

9 ለዚሁ፣ የሙታንና የሕያዋን ጌታ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ ሞቶአል፤ በሕይወትም ተነሥቶአል።

10 ታዲያ አንተ በወንድምህ ላይ ለምን ትፈርዳለህ? ለምንስ ወንድምህን ትንቃለህ? ሁላችንም በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት እንቀርባለንና፤

11 እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤“ ‘እኔ ሕያው ነኝና’፤‘ጒልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር ይመሰክራል’ ” ይላል ጌታ።

12 ስለዚህ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን።

13 ስለዚህ እርስ በርሳችን፣ አንዱ በሌላው ላይ ከመፍረድ እንቈጠብ፤ በዚህ ፈንታ ግን በወንድምህ መንገድ ላይ የማሰናከያ ድንጋይ ወይም ወጥመድ እንዳታስቀምጥ ቊርጥ ሐሳብ አድርግ።

14 በጌታ በኢየሱስ ሆኜ በራሱ ንጹሕ ያልሆነ ምንም ምግብ እንደሌለ ተረድቻለሁ፤ ነገር ግን አንድ ሰው አንድን ነገር ንጹሕ እንዳልሆነ የሚቈጥር ከሆነ፣ ያ ነገር ለእርሱ ንጹሕ አይደለም።

15 ወንድምህ በምትበላው ምግብ የሚያዝን ከሆነ፣ በፍቅር አልተመላለስህም፤ ክርስቶስ የሞተለትን ወንድምህን በመብልህ አታጥፋው።

16 መልካም ነው ብለህ የምታስበው ነገር ክፉ ተብሎ እንዲነቀፍ አታድርግ።

17 የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም፣ በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ሐሤት ነው እንጂ፣ የመብልና የመጠጥ ጒዳይ አይደለም፤

18 በዚህ ሁኔታ ክርስቶስን የሚያገለግል እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛልና፤ በሰውም ዘንድ የተመሰገነ ነው።

19 ስለዚህ ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችንም የምንተናነጽበትን ማንኛውንም ጥረት እናድርግ።

20 ለምግብ ስትል የእግዚአብሔርን ሥራ አታፍርስ። ሁሉ ንጹሕ ነው፤ ነገር ግን ለሌላው ሰው የመሰናከያ ምክንያት የሚሆነውን መብላት ስሕተት ነው።

21 ለወንድምህ መሰናከል ምክንያት የሚሆነውን ሥጋን አለመብላት፣ ወይንን አለ መጠጣት፣ ወይም አንዳች ነገርን አለማድረግ መልካም ነው።

22 እንግዲያስ ስለ እነዚህ ነገሮች ያለህ እምነት በአንተና በእግዚአብሔር መካከል የተጠበቀ ይሁን፤ ትክክል ነው ብሎ በተቀበለው ነገር ራሱን የማይኰንን የተባረከ ሰው ነው።

23 ነገር ግን የሚጠራጠር ሰው ቢበላ በእምነት ስላልሆነ፣ ተፈርዶበታል፤ በእምነት ያልተደረገ ሁሉ ኀጢአት ነውና።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16