1 ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላሉት ሹማምት መገዛት ይገባዋል፤ ከእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣናት በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው።
2 ስለዚህ፣ በባለ ሥልጣን ላይ የሚያምፅ በእግዚአብሔር ሥርዐት ላይ ማመፁ ነው፤ ይህን የሚያደርጉትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ያመጣሉ።
3 ገዦች ክፉ ለሚሠሩ እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና። ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትፈልጋለህን? እንግዲያስ መልካሙን አድርግ፤ እርሱም ያመሰግንሃል፤
4 እርሱ ለአንተ መልካሙን ለማድረግ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። ነገር ግን ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ምክንያቱም ሰይፉን በከንቱ አልታጠቀም፤ ክፉ የሚያደርገውን ለመቅጣት የቊጣ መሣሪያ የሆነ፣ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው።
5 ስለዚህም ቅጣትን በመፍራት ብቻ ሳይሆን፣ ለኅሊና ሲባል ለባለ ሥልጣናት መገዛት ተገቢ ነው።
6 ግብር የምትከፍሉትም ደግሞ ለዚህ ነው፤ ባለ ሥልጣናቱ፣ በዚሁ ተግባር ላይ የተሠማሩ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸውና፤
7 ለእያንዳንዱ የሚገባውን ስጡ፤ ግብር ከሆነ ግብርን፣ ቀረጥ ከሆነም ቀረጥን፣ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባውም ክብርን ስጡ።
8 እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር የማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤ ባልንጀራውን የሚወድ እርሱ ሕግን ፈጽሞአልና።
9 “አታመንዝር”፣ “አትግደል”፣ “አትስረቅ”፣ “አትመኝ” የሚሉትና ሌሎችም ትእዛዛት ቢኖሩም፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” በሚለው በዚህ በአንድ ሕግ ተጠቃለዋል።
10 ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ መፈጸሚያ ነው።
11 ዘመኑን በማስተዋል ይህን አድርጉ፤ ከእንቅልፋችሁ የምትነቁበት ጊዜ አሁን ነው፤ መዳናችን መጀመሪያ ካመንበት ጊዜ ይልቅ አሁን ወደ እኛ ቀርቦአልና።
12 ሌሊቱ ሊያልፍ፣ ቀኑም ሊጀምር ነው። ስለዚህ የጨለማን ሥራ ጥለን፣ የብርሃንን ጦር ዕቃ እንልበስ።
13 በቀን እንደምንመላለስ በአግባብ እንመላለስ። በጭፈራና በስካር አይሁን፤ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፤ በክርክርና በቅናትም አይሁን።
14 ይልቁንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም ይፈጽም ዘንድ ለሥጋ በሐሳባችሁ አትመቻቹለት።