ሮሜ 6 NASV

ለኀጢአት መሞት፣ በክርስቶስ ሕያው መሆን

1 እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ ኀጢአት እየሠራን እንኑር?

2 ከቶ አይሆንም፤ ለኀጢአት ሞተናል፤ ታዲያ እንዴት አድርገን ከእንግዲህ በእርሱ እንኖራለን?

3 ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንድንሆን የተጠመቅን፣ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?

4 ስለዚህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሞት እንደ ተነሣ፣ እኛም እንዲሁ በአዲስ ሕይወት እንድንኖር በጥምቀት ሞተን ከእርሱ ጋር ተቀብረናል።

5 በሞቱ ከእርሱ ጋር እንደዚህ ከተባበርን፣ በትንሣኤው ደግሞ በርግጥ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን።

6 ከእንግዲህ የኀጢአት ባሮች እንዳንሆን፣ የኀጢአት ሰውነት እንዲሻር አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤

7 ምክንያቱም የሞተ ከኀጢአት ነጻ ወጥቶአል።

8 ከክርስቶስ ጋር ከሞትን፣ ከእርሱ ጋር እንደምንኖር እናምናለን።

9 ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶአልና፣ ዳግመኛ እንደማይሞት እናውቃለንና፤ ሞት ከእንግዲህ በእርሱ ላይ ጒልበት አይኖረውም።

10 በሞተ ጊዜ፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለኀጢአት ሞቶአል፤ ነገር ግን በሕይወት መኖርን ለእግዚአብሔር ይኖራል።

11 እንደዚሁም ለኀጢአት እንደ ሞታችሁ፣ ነገር ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደሆናችሁ ራሳችሁን ቊጠሩ።

12 ስለዚህ ክፉ መሻቱን ትፈጽሙ ዘንድ በሟች ሥጋችሁ ላይ ኀጢአት እንዲነግሥበት አታድርጉ።

13 ብልቶቻችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኀጢአት አታቅርቡ፤ ይልቁንስ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።

14 ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላልሆናችሁ፣ ኀጢአት አይገዛችሁምና።

የጽድቅ ባሮች

15 እንግዲህ ምን ይሁን? ከሕግ በታች ሳይሆን፣ ከጸጋ በታች በመሆናችን ኀጢአት እንሥራን? በጭራሽ አይገባም!

16 ራሳችሁን እንደ ባሪያ አድርጋችሁ ስታቀርቡ፣ ለምት ታዘዙት ለእርሱ፣ ይኸውም ወደ ሞት ለሚወስደው ለኀጢአት ወይም ወደ ጽድቅ ለሚያደርሰው ለመታዘዝ ባሮች እንደሆናችሁ አታውቁምን?

17 ነገር ግን የኀጢአት ባሮች የነበራችሁ ቢሆንም፣ ለተሰጣችሁለት ትምህርት በሙሉ ልብ የታዘዛችሁ በመሆናችሁ፣ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤

18 ከኀጢአት ነጻ ወጥታችሁ፣ የጽድቅ ባሪያዎች ሆናችኋል።

19 በተፈጥሮ ደካሞች ስለ ሆናችሁ፣ በሰው ቋንቋ ይህን እላለሁ፤ ብልቶቻችሁን በባርነት ለርኵሰትና እየባሰ ለሚሄድ ክፋት ታቀርቡ እንደ ነበር፣ አሁን ደግሞ ወደ ቅድስና ለሚወስደው ጽድቅ ባሪያ አድርጋችሁ አቅርቡ።

20 የኀጢአት ባሮች ሳላችሁ ከጽድቅ ነጻ ነበራችሁ።

21 አሁን ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ጥቅም አገኛችሁ? የዚያ ነገር ውጤት ሞት ነው።

22 አሁን ግን ከኀጢአት ነጻ ወጥታችሁ የእግዚአብሔር ባሮች ሆናችኋል፤ የምትሰበስቡትም ፍሬ ወደ ቅድስና ያመራል፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው።

23 የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16