ሮሜ 12 NASV

ሕያው መሥዋዕት

1 እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኮአችሁ ነው።

2 መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።

3 እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችሁ በሰጣችሁ እምነት መጠን ራሳችሁን በአግባቡ መዝኑ እንጂ፣ ከሆናችሁት በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ በተሰጠኝ ጸጋ እያንዳንዳችሁን እመክራለሁ።

4 እያንዳንዳችን በአንዱ አካላችን ብዙ ብልቶች እንዳሉን፣ እነዚህም ብልቶች አንድ ዐይነት ተግባር እንደሌላቸው ሁሉ፣

5 እንዲሁም እኛ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን። እያንዳንዳችንም የሌላው ብልት ነን።

6 እንደ ተሰጠን ጸጋ የተለያዩ ስጦታዎች አሉን፤ ለአንዱ የተሰጠው ስጦታ ትንቢት መናገር ከሆነ፣ እንደ እምነቱ መጠን ይናገር።

7 ማገልገል ቢሆን ያገልግል፤ ማስተማርም ከሆነ ያስተምር፤

8 መምከር ከሆነ ይምከር፤ ለሌላቸው መለገስ ከሆነም አብዝቶ ይለግስ፤ ማስተዳደር ከሆነም በትጋት ያስተዳድር፤ ምሕረት ማድረግ ከሆነም በደስታ ይማር።

ፍቅር

9 ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን፤ ክፉ የሆነውን ሁሉ ተጸየፉ፤ በጎ ከሆነው ነገር ጋር ተቈራኙ።

10 እርስ በርሳችሁ በወንድማማች መዋደድ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፤ አንዱ ሌላውን ከራሱ በማስበለጥ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ።

11 ጌታን ለማገልገል በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ እንጂ ከዚህ ትጋት ወደ ኋላ አትበሉ።

12 በተስፋ ደስተኞች ሁኑ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ።

13 ችግረኛ ለሆኑ ቅዱሳን ካላችሁ አካፍሉ፤ እንግዶችን ተቀበሉ።

14 የሚያሳድዷችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ።

15 ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያዝኑም ጋር እዘኑ።

16 እርስ በርሳችሁ በመስማማት ኑሩ። ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ጋር አብራችሁ ለመሆን ፍቀዱ እንጂ አትኵራሩ፤ በራሳችሁም አትመኩ።

17 ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ትጉ።

18 ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።

19 ወዳጆቼ ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ቊጣ ፈንታ ስጡ እንጂ አትበቀሉ፤ “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።

20 ይልቁንስ፣“ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ቢጠማም አጠጣው።ይህን በማድረግህም የእሳት ፍም በራሱ ላይ ትከምራለህ።”

21 ክፉን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16