ሮሜ 9 NASV

የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ምርጫ

1 በክርስቶስ ሆኜ እውነት እናገራለሁ፤ አልዋሽም፤ ኅሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል።

2 ታላቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ጭንቀት በልቤ አለ።

3 ለወገኖቼ ስል ስለ ወንድሞቼ እኔ ራሴ የተረገምሁና ከክርስቶስም ተለይቼ የተጣልሁ እንድሆን እንኳ እወድ ነበር፤

4 እነርሱም የእስራኤል ሕዝብ ናቸው፤ ልጅ መሆን፣ መለኮታዊ ክብር፣ ኪዳን፣ ሕግን መቀበል፣ የቤተ መቅደስ ሥርዐትና ተስፋ የእነርሱ ናቸውና።

5 አባቶችም የእነርሱ ናቸው፤ ክርስቶስም በሥጋ የትውልድ ሐረጉ የሚቈጠረው ከእነርሱ ነው፤ እርሱም፣ ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘላለም የተመሰገነ አምላክ ነው፤ አሜን።

6 ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ተሽሮአል ማለት አይደለም፤ ከእስራኤል የተወለደ ሁሉ እስራኤላዊ አይደለምና።

7 ከአብርሃም ዘርም ስለሆኑ፣ ሁሉም ልጆቹ አይደሉም፤ ይልቁንስ፣ “ትውልድህ በይሥሐቅ በኩል ይጠራልሃል” እንደ ተባለው ነው።

8 ይህም ማለት የእግዚአብሔር ልጆች የተባሉት የሥጋ ልጆች አይደሉም፤ ነገር ግን የአብርሃም ልጆች የተባሉት የተስፋው ልጆች ናቸው።

9 “ጊዜው ሲደርስ እመለሳለሁ፤ ሳራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች” ተብሎ ተስፋው ተሰጥቶአልና።

10 ይህም ብቻ ሳይሆን፣ የርብቃ ልጆች አንድ አባት አላቸው፤ እርሱም አባታችን ይሥሐቅ ነው።

11 መንትዮቹ ገና ሳይወለዱ፣ ወይም በጎም ሆነ ክፉ ሳያደርጉ፣ የእግዚአብሔር ሐሳብ በምርጫ ይጸና ዘንድ፣

12 በሥራ ሳይሆን ከጠሪው በመሆኑ፣ “ታላቁ ታናሹን ያገለግላል” ተብሎ ተነገራት።

13 ይህም፣ “ያዕቆብን ወደድሁ፤ ዔሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።

14 እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር አድልዎ ያደርጋልን? በፍጹም አያደርግም!

15 ለሙሴ፣“የምምረውን እምረዋለሁ፤ለምራራለትም እራራለታለሁ” ይላልና።

16 እንግዲህ ይህ ከሰው ፍላጎት ወይም ጥረት ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው።

17 መጽሐፍ ፈርዖንን፣ “ኀይሌ በአንተ እንዲታይ፣ ስሜም በምድር ሁሉ እንዲነገር ለዚህ አስነሣሁህ” ይላልና።

18 ስለዚህ እግዚአብሔር ሊምረው ለሚወደው ምሕረት ያደርግለታል፤ ልቡ እንዲደነድን የፈለገውንም ያደነ ድነዋል።

19 ከእናንተ አንዱ፣ “ታዲያ እንደዚህ ከሆነ እግዚአብሔር እስከ አሁን ለምን ይወቅሰናል? ምክንያቱም ፈቃዱን ሊቋቋም የሚችል ማን አለ?” ይለኝ ይሆናል።

20 ነገር ግን ለእግዚአብሔር መልስ የምትሰጥ አንተ ማን ነህ? “ሥራ ሠሪውን፣ ‘ለምን እንዲህ ሠራኸኝ?’ ይለዋልን?”

21 ሸክላ ሠሪ፣ ከሚሠራው ጭቃ፣ አንዳንዱን ሸክላ ለክብር፣ ሌላውን ደግሞ ለተራ አገልግሎት የማድረግ መብት የለውምን?

22 እግዚአብሔር ቊጣውን ለማሳየት፣ ኀይሉንም ለማሳወቅ ፈልጎ የቍጣው መግለጫ የሆኑትን፣ ለጥፋትም የተዘጋጁትን እጅግ ታግሦ ቢሆንሳ!

23 አስቀድሞ ለክብር ላዘጋጃቸው፣ የምሕረቱም መግለጫዎች ለሆኑት፣ የክብሩ ባለጠግነት እንዲታወቅ ይህን አድርጎ እንደሆነስ?

24 የጠራው ከአይሁድ ወገን ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብ ወገን የሆነውን እኛን እንኳ ሳይቀር አይደለምን?

25 በሆሴዕ እንዲህ እንደሚል፤“ሕዝቤ ያልሆኑትን፣ ‘ሕዝቤ’ ብዬ እጠራቸዋለሁ”፤ያልተወደደችውንም ‘የተወደደችው’ ብዬ እጠራለሁ።

26 ደግሞም፣ “ ‘ሕዝቤ አይደላችሁም’፤ተብሎ በተነገራቸው በዚያ ቦታ፣‘የሕያው እግዚአብሔር ልጆች’ ተብለውይጠራሉ።”

27 ኢሳይያስም ስለ እስራኤል እንዲህ ሲል ይጮኻል፤“የእስራኤል ልጆች ቊጥር በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ቢሆንም፣ትሩፉ ብቻ ይድናል።

28 ጌታ ፍርዱን በምድር ላይ፣በፍጥነትና ለመጨረሻ ጊዜ ይፈጽማልና።”

29 ይኸውም ቀደም ሲል ኢሳይያስእንደ ተናገረው ነው፤“የሰራዊት ጌታ፣ ዘር ባያስቀርልን ኖሮ፣እንደ ሰዶም በሆን ነበር፤ገሞራንም በመሰልን ነበር።”

የእስራኤል አለማመን

30 እንግዲህ ምን እንበል? በእምነት የሆነውን ጽድቅ፣ ለጽድቅ ያልደከሙት አሕዛብ አገኙት፤

31 ነገር ግን የጽድቅን ሕግ የተከታተሉት እስራኤል አላገኙትም።

32 ይህ ለምን ሆነ? በእምነት ሳይሆን በሥራ እንደሆነ አድርገው በመቊጠር ስለ ተከታተሉት ነው፤ እነርሱም፣ “በማሰናከያው ድንጋይ” ተሰናከሉ።

33 ይህም፣“እነሆ፤ ሰዎችን እንዲደናቀፉ የሚያደርግ ድንጋይ፣እንዲወድቁ የሚያደርግ ዐለት፣በጽዮን ላይ አስቀምጣለሁ፤ በእርሱም የሚያምን አያፍርም”ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16