4 እነርሱም የእስራኤል ሕዝብ ናቸው፤ ልጅ መሆን፣ መለኮታዊ ክብር፣ ኪዳን፣ ሕግን መቀበል፣ የቤተ መቅደስ ሥርዐትና ተስፋ የእነርሱ ናቸውና።
5 አባቶችም የእነርሱ ናቸው፤ ክርስቶስም በሥጋ የትውልድ ሐረጉ የሚቈጠረው ከእነርሱ ነው፤ እርሱም፣ ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘላለም የተመሰገነ አምላክ ነው፤ አሜን።
6 ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ተሽሮአል ማለት አይደለም፤ ከእስራኤል የተወለደ ሁሉ እስራኤላዊ አይደለምና።
7 ከአብርሃም ዘርም ስለሆኑ፣ ሁሉም ልጆቹ አይደሉም፤ ይልቁንስ፣ “ትውልድህ በይሥሐቅ በኩል ይጠራልሃል” እንደ ተባለው ነው።
8 ይህም ማለት የእግዚአብሔር ልጆች የተባሉት የሥጋ ልጆች አይደሉም፤ ነገር ግን የአብርሃም ልጆች የተባሉት የተስፋው ልጆች ናቸው።
9 “ጊዜው ሲደርስ እመለሳለሁ፤ ሳራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች” ተብሎ ተስፋው ተሰጥቶአልና።
10 ይህም ብቻ ሳይሆን፣ የርብቃ ልጆች አንድ አባት አላቸው፤ እርሱም አባታችን ይሥሐቅ ነው።