1 በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ወደ ሞሬታዊው ወደ ሚክያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል፣ ስለ ሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ራእይ ይህ ነው፤
2 እናንተ አሕዛብ ሆይ፤ ሁላችሁም ስሙ፤ምድር ሆይ፤ በውስጧም የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ፤ጌታ ከቅዱስ መቅደሱ፣ልዑል እግዚአብሔር በእናንተ ላይ ይመሰክርባችኋል።
3 እነሆ፤ እግዚአብሔር ከመኖሪያ ስፍራው ይመጣል፤ወርዶም በምድር ከፍታዎች ላይ ይራመዳል።
4 ተራሮች ከሥሩ ይቀልጣሉ፤ሸለቆዎችም ይሰነጠቃሉ፤በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፣በገደል ላይ እንደሚወርድ ፈሳሽ ይሆናሉ።
5 ይህ ሁሉ የሚሆነው ስለ ያዕቆብ በደል፣ስለ እስራኤልም ቤት ኀጢአት ነው።የያዕቆብ በደል ምንድን ነው?ሰማርያ አይደለችምን?የይሁዳስ የኰረብታ መስገጃ ምንድን ነው?ኢየሩሳሌም አይደለችምን?
6 “ስለዚህ ሰማርያን የፍርስራሽ ክምር፣ወይን የሚተከልባትም ስፍራ አደርጋታለሁ፤ድንጋዮቿን ወደ ሸለቆ አወርዳለሁ፤መሠረቷንም ባዶ አደርጋለሁ።
7 ጣዖቶችዋ ሁሉ ይሰባበራሉ፤ለቤተ መቅደሷ የቀረበው ገጸ በረከት በእሳት ይቃጠላል፤ምስሎችዋን ሁሉ እደመስሳለሁ፤ገጸ በረከቷን በዝሙት አዳሪነት እንደ ሰበሰበች ሁሉ፣አሁንም ገጸ በረከትዋ የዝሙት አዳሪነት ዋጋ መቀበያ ይሆናል።