1 የእስራኤል ንጉሥ፣ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሌዎች፤
2 ጥበብንና ተግሣጽን ለመቀበል፤ጥልቅ ሐሳብ የሚገልጡ ቃላትን ለማስተዋል፤
3 ጽድቅን፣ ፍትሕንና ሚዛናዊ ብያኔን በማድረግ፣የተገራ ጠቢብ ልቦናን ለማግኘት፤
4 ብስለት ለሌላቸው አስተዋይነትን፣በዕድሜ ለጋ ለሆኑት ዕውቀትንና ልባምነትን ለመስጠት፤
5 ጥበበኞች ያድምጡ፤ ትምህርታቸውንም ያዳብሩ፤አስተዋዮችም መመሪያ ያግኙበት፤
6 ይህም የጠቢባንን ምሳሌዎችንና ተምሳሌቶችን፣አባባሎችንና ዕንቆቅልሾችን ይረዱ ዘንድ ነው።
7 እግዚአብሔርን መፍራት የዕውቀት መጀመሪያ ነው፤ተላሎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ።
8 ልጄ ሆይ፤ የአባትህን ምክር አድምጥ፤የእናትህንም ትምህርት አትተው።
9 ለራስህ ሞገስን የሚያጐናጽፍ አክሊል፣ዐንገትህን የሚያስውብ ድሪ ይሆንልሃል።
10 ልጄ ሆይ፤ ኀጢአተኞች ቢያባብሉህ፣እሺ አትበላቸው፤
11 “ከእኛ ጋር ናና፣ ደም ለማፍሰስ እናድባ፤በደል በሌለበት ሰው ላይ እንሸምቅ፤
12 እንደ መቃብር፣ ወደ ጒድጓድ እንደሚወርዱ፣ከነሕይወታቸው እንዳሉ እንዋጣቸው፤
13 ውድ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ በያይነቱ እናገኛለን፤ቤቶቻችንንም በዝርፊያ እንሞላለን፤
14 ከእኛ ጋር ዕጣህን ጣል፤የጋራ ቦርሳ ይኖረናልቃ ቢሉህ፣
15 ልጄ ሆይ፤ አብረሃቸው አትሂድ፤በሚሄዱበትም መንገድ እግርህን አታንሣ፤
16 እግራቸው ወደ ኀጢአት ይቸኵላል፤ደም ለማፍሰስም ፈጣኖች ናቸው።
17 ወፎች ፊት እያዩ ወጥመድ መዘርጋት፣ምንኛ ከንቱ ነው!
18 እነዚህ ሰዎች የሚያደቡት በገዛ ደማቸው ላይ ነው፤የሚሸምቁትም በራሳቸው ላይ ብቻ ነው።
19 ያላግባብ ለጥቅም የሚሯሯጡ ሁሉ መጨረሻቸው እንዲህ ነው፤የሕይወታቸው መጥፊያም ይኸው ነው።
20 ጥበብ በጐዳና ላይ ጮኻ ትጣራለች፤በየአደባባዩ ድምፅዋን ከፍ ታደርጋለች፤
21 ዉካታ በበዛባቸው ጐዳናዎች ላይ ትጮኻለች፤በከተማዪቱም መግቢያ በር ላይ እንዲህ ትላለች፤
22 “እናንት ብስለት የሌላችሁ ማስተዋል የሌለበት መንገዳችሁን እስከ መቼ ትወዱታላችሁ?ፌዘኞች በፌዝ ደስ የሚሰኙት፣ሞኞችስ ዕውቀትን የሚጠሉት እስከ መቼ ነው?
23 ዘለፋዬን ብትሰሙኝ ኖሮ፣ልቤን ባፈሰስሁላችሁ፣ሐሳቤንም ባሳወቅኋችሁ ነበር።
24 ነገር ግን በተጣራሁ ጊዜ እምቢ ስላላችሁኝ፣እጄንም ስዘረጋ ማንም ግድ ስላልነበረው፣
25 ምክሬን ሁሉ ስለናቃችሁ፣ዘለፋዬንም ስላልተቀበላችሁ፣
26 እኔ ደግሞ በመከራችሁ እሥቅባችኋለሁ፤መዓት በሚወርድባችሁም ጊዜ አፌዝባችኋለሁ፤
27 መዓት እንደ ማዕበል ሲያናውጣችሁ፣መከራም እንደ ዐውሎ ነፋስ ሲጠራርጋችሁ፣ሥቃይና ችግር ሲያጥለቀልቃችሁ አፌዝባችኋለሁ።
28 “በዚያን ጊዜ ይጠሩኛል፤ እኔ ግን አልመልስላቸውም፤አጥብቀው ይፈልጉኛል፤ ነገር ግን አያገኙኝም።
29 ዕውቀትን ስለ ጠሉ፣ እግዚአብሔርንም መፍራት ስላልመረጡ፣
30 ምክሬን ለመቀበል ስላልፈለጉ፣ዘለፋዬን ስለናቁ፣
31 የመንገዳቸውን ፍሬ ይበላሉ፤የዕቅዳቸውንም ውጤት ይጠግባሉ።
32 ብስለት የሌላቸውን ስድነታቸው ይገድላቸዋል፤ተላሎችንም ቸልተኝነታቸው ያጠፋቸዋል፤
33 የሚያዳምጠኝ ሁሉ ግን በሰላም ይኖራል፤ክፉን ሳይፈራ ያለ ሥጋት ይቀመጣል።”