ምሳሌ 16 NASV

1 የልብ ዕቅድ የሰው ነው፤የአንደበት መልስ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

2 ለሰው መንገዱ ሁሉ ንጹሕ መስሎ ይታየዋል፤መነሻ ሐሳቡ ግን በእግዚአብሔር ይመዘናል።

3 የምታደርገውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ዕቅድህም ሁሉ ይሳካልሃል።

4 እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ለራሱ ዐላማ ሠርቶአል፤ክፉዎችንም እንኳ ለጥፋት ቀን አዘጋጅቶአል።

5 እግዚአብሔር በልብ የሚታበዩትን ሁሉ ይጸየፋል፤እነርሱም ከቅጣት እንደማያመልጡ በርግጥ ዕወቅ።

6 በፍቅርና በታማኝነት ኀጢአት ይሰረያል፤ እግዚአብሔርን በመፍራት ሰው ከክፋት ይርቃል።

7 የሰው መንገድ እግዚአብሔርን ደስ ሲያሰኘው፣ጠላቶቹ እንኳ አብረውት በሰላም እንዲኖሩ ያደርጋል።

8 ከጽድቅ ጋር ጥቂቱ ነገር፣በግፍ ከሚገኝ ብዙ ትርፍ ይሻላል።

9 ሰው በልቡ መንገዱን ያቅዳል፤ እግዚአብሔር ግን ርምጃውን ይወስንለታል።

10 የንጉሥ ከንፈሮች እንደ አምላክ ቃል ይናገራሉ፤አንደበቱ ፍትሕን ያዛባ ዘንድ አይገባም።

11 ሐቀኛ መስፈሪያና ሚዛን ከእግዚአብሔር ናቸው፤በከረጢት ውስጥ ያሉት መመዘኛዎችም ሁሉ ሥራዎቹ ናቸው።

12 ክፋትን ማድረግ ለነገሥታት አጸያፊ ነው፤ዙፋን የሚጸናው በጽድቅ ነውና።

13 ነገሥታት በታማኝ ከንፈሮች ደስ ይላቸዋል፤እውነት የሚናገረውን ሰው ይወዱታል።

14 የንጉሥ ቊጣ የሞት መልእክተኛ ነው፤ጠቢብ ሰው ግን ቊጣውን ያበርዳል።

15 የንጉሥ ፊት ሲፈካ ሕይወት አለ፤በጎነቱም ዝናብ እንዳዘለ የበልግ ደመና ነው።

16 ከወርቅ ይልቅ ጥበብን ማግኘት፣ከብርም ማስተዋልን መምረጥ ምንኛ ይበልጣል!

17 የቅኖች ጐዳና ከክፋት የራቀ ነው፤መንገዱንም የሚጠብቅ ሕይወቱን ይጠብቃል።

18 ትዕቢት ጥፋትን፣የእብሪት መንፈስም ውድቀትን ትቀድማለች።

19 በተዋረደ መንፈስ ከተጨቈኑት ጋር መሆን፣ከትዕቢተኞች ጋር ብዝበዛን ከመካፈል ይሻላል።

20 ምክርን የሚሰማ ይለመልማል፤ በእግዚአብሔርም የሚታመን ቡሩክ ነው።

21 ልባቸው ጠቢብ የሆነ አስተዋዮች ይባላሉ፤ደስ የሚያሰኙ ቃላትም ዕውቀትን ያዳብራሉ።

22 ማስተዋልን ገንዘብ ላደረጋት የሕይወት ምንጭ ናት፤ቂልነት ግን በተላሎች ላይ ቅጣት ታመጣባቸዋለች።

23 የጠቢብ ሰው ልብ አንደበቱን ይመራል፤ከንፈሮቹም ዕውቀትን ያዳብራሉ።

24 ደስ የሚያሰኝ ቃል የማር ወለላ ነው፤ለነፍስ ጣፋጭ፣ ለዐጥንትም ፈውስ ነው።

25 ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ይመራል፤

26 ሠራተኛን የዕለት ጒርስ ፍላጎቱ ታታሪ ያደርገዋል፤ራቡም ይገፋፋዋል።

27 ወራዳ ሰው ክፋትን ያውጠነጥናል፤ንግግሩም እንደሚለበልብ እሳት ነው።

28 ጠማማ ሰው ጠብን ይዘራል፤ሐሜተኛም የቅርብ ወዳጆችን ይለያያል።

29 ክፉ ሰው ባልንጀራውን ያባብለዋል፤መልካም ወዳልሆነውም መንገድ ይመራዋል።

30 በዐይኑ የሚጠቅስ ሰው ጠማማነትን ያውጠነጥናል፤በከንፈሩ የሚያሽሟጥጥም ወደ ክፋት ያዘነብላል።

31 ሽበት የክብር ዘውድ ነው፤የሚገኘውም በጽድቅ ሕይወት ነው።

32 ታጋሽ ሰው ከጦረኛ፣ስሜቱን የሚገዛም ከተማን በጒልበቱ ከሚይዝ ይበልጣል።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31