ምሳሌ 3 NASV

ከጥበብ የሚገኝ ተጨማሪ በረከት

1 ልጄ ሆይ፤ ትምህርቴን አትርሳ፤ትእዛዛቴን በልብህ ጠብቅ፤

2 ቀኖችን ይጨምሩልሃል፤ ዓመቶችንም ያረዝሙልሃል፤ሕይወት፣ ሀብትንና ሰላምን ያበዙልሃል።

3 ፍቅርና ታማኝነት ከቶ አይለዩህ፤በዐንገትህ ዙሪያ እሰራቸው፤በልብህም ጽላት ላይ ጻፋቸው።

4 በዚያን ጊዜ ሞገስንና መልካም ስምን፣በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ ታገኛለህ።

5 በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤

6 በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።

7 በራስህ አስተያየት ጠቢብ ነኝ አትበል፤ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ከክፉም ራቅ።

8 ይህም ለሰውነትህ ጤንነትን፣ለዐጥንትህም ልምላሜን ያመጣልሃል።

9 እግዚአብሔርን በሀብትህ፣ከምርትህ ሁሉ በኵራት አክብረው፤

10 ይህን ብታደርግ፣ ጎተራህ ሞልቶ ይትረፈረፋል፤መጥመቂያህም በአዲስ የወይን ጠጅ ቲፍ ብሎ ይሞላል።

11 ልጄ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፤በዘለፋውም አትመረር፤

12 አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣ ሁሉ፣ እግዚአብሔርም የሚወደውን ይገሥጻልና።

13 ጥበብን የሚያገኛት፣ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርጋት ሰው ቡሩክ ነው፤

14 እርሷ ከብር ይልቅ ትርፍ የምታመጣ፣ከወርቅም ይልቅ ጥቅም የምታስገኝ ናትና።

15 ከቀይ ዕንቍ ይበልጥ ውድ ናት፤አንተ ከምትመኘውም ሁሉ የሚስተካከላት የለም።

16 በቀኝ እጇ ረጅም ዕድሜ አለ፤በግራ እጇም ሀብትና ክብር ይዛለች።

17 መንገዷ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ጐዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው።

18 ለሚያቅፏት የሕይወት ዛፍ ናት፤የሚይዟትም ይባረካሉ።

19 እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፤በማስተዋል ሰማያትን በየስፍራቸው አጸና፤

20 በዕውቀቱ ቀላያት ተከፈሉ፤ደመናትም ጠልን አንጠበጠቡ።

21 ልጄ ሆይ፤ ትክክለኛ ፍርድንና አስተውሎ መለየትን ጠብቅ፤እነዚህ ከእይታህ አይራቁ፤

22 ለነፍስህ ሕይወት፣ለዐንገትህም ጌጥ ይሆናሉ።

23 ከዚያም መንገድህን በሰላም ትሄዳለህ፤እግርህም አይሰናከልም፤

24 ስትተኛ አትፈራም፤ትተኛለህ እንቅልፍህም ጣፋጭ ይሆናል።

25 ድንገተኛን መከራ፣በክፉዎች ላይ የሚደርሰውንም ጥፋት አትፍራ፤

26 እግዚአብሔር መታመኛህ ይሆናልና፤እግርህንም በወጥመድ ከመያዝ ይጠብቃል።

27 ማድረግ እየቻልህለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ አትቈጠብ።

28 አሁን በእጅህ እያለ፣ጎረቤትህን፣ “ቈይተህ ተመለስ፤ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው።

29 አንተን ተማምኖ በአጠገብህ በተቀመጠ፣በጎረቤትህ ላይ ክፉ አትምከርበት።

30 ምንም ጒዳት ሳያደርስብህ፣ያለ ምክንያት ሰውን አትክሰስ።

31 በክፉ ሰው አትቅና፤የትኛውንም መንገዱን አትምረጥ፤

32 እግዚአብሔር ጠማማን ሁሉ ይጸየፋልና፤ለቅን ሰው ግን ምስጢሩን ይገልጥለታል።

33 የእግዚአብሔር ርግማን በክፉዎች ቤት ላይ ነው፤የጻድቃንን ቤት ግን ይባርካል።

34 እርሱ በዕቡያን ፌዘኞች ላይ ያፌዛል፤ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል።

35 ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤ሞኞችን ግን ለውርደት ያጋልጣቸዋል።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31