ምሳሌ 24 NASV

1 በክፉ ሰዎች አትቅና፤ጓደኝነታቸውም አይመርህ፤

2 ልባቸው ዐመፅን ያውጠነጥናልና፤ከንፈራቸውም ሸፍጥ ያወራል።

3 ቤት በጥበብ ይሠራል፤በማስተዋልም ይጸናል፤

4 በዕውቀትም ውድና ውብ በሆነ ንብረት፣ክፍሎቹ ይሞላሉ።

5 ጠቢብ ሰው ታላቅ ኀይል አለው፤ዕውቀት ያለውም ሰው ብርታትን ይጨምራል፤

6 ጦርነት ለመግጠም መልካም ምክር፣ድል ለማድረግም ብዙ አማካሪዎች ያስፈልጋሉ።

7 ጥበብ ለተላላ በጣም ሩቅ ናት፤በከተማዪቱ በር ሸንጎ ላይም መናገር አይችልም።

8 ክፋት የሚያውጠነጥን፣‘ተንኰለኛ’ በመባል ይታወቃል።

9 የተላላ ዕቅድ ኀጢአት ነው፤ሰዎችም ፌዘኛን ይጸየፋሉ።

10 በመከራ ጊዜ ፈራ ተባ ካልህ፣ዐቅምህ ምንኛ ደካማ ነው!

11 ወደ ሞት የሚነዱትን ታደጋቸው፤እየተጐተቱ ለዕርድ የሚሄዱትን አድናቸው።

12 አንተም፣ “ስለዚህ ነገር ምንም አላውቅም” ብትል፣ልብን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን?ሕይወትህን የሚጠብቃት እርሱ አያውቅምን?ለእያንዳንዱስ እንደ ሥራው መጠን አይከፍለውምን?

13 ልጄ ሆይ፤ መልካም ነውና ማር ብላ፤የማር ወለላም ጣዕም ይጣፍጥሃል።

14 ጥበብም ለነፍስህ እንደዚሁ ጣፋጭ እንደሆነች ዕወቅ፤ብታገኛት ለነገ አለኝታ ይኖርሃል፤ተስፋህም ከንቱ አይሆንም።

15 በጻድቅ ሰው ቤት ላይ እንደ ወንበዴ አታድፍጥ፤መኖሪያውንም በድንገት አታጥቃ፤

16 ጻድቅ ሰባት ጊዜ እንኳ ቢወድቅ ይነሣልና፤ክፉዎች ግን በጥፋት ይወድቃሉ።

17 ጠላትህ ሲወድቅ ደስ አይበልህ፤ሲሰናከልም ልብህ ሐሤት አያድርግ፤

18 አለዚያ እግዚአብሔር ይህን አይቶ ደስ አይለውም፤ቍጣውንም ከእርሱ ይመልሳል።

19 በጨካኞች ድርጊት አትጨነቅ፤በክፉዎችም አትቅና፤

20 ግፈኛ ተስፋ የለውምና፤የክፉዎችም መብራት ድርግም ብላ ትጠፋለች።

21 ልጄ ሆይ፤ እግዚአብሔርንና ንጉሥን ፍራ፤ከዐመፀኞችም ጋር አትተባበር፤

22 ሁለቱም የሚያመጡት መዓት፤ምን እንደሚሆን ማን ያውቃል?

ተጨማሪ የጠቢባን ምሳሌዎች

23 እነዚህም ደግሞ የጠቢባን ምሳሌዎች ናቸው፦በዳኝነት አድልዎ ማድረግ ተገቢ አይደለም፤

24 በደለኛውን፣ “አንተ ንጹሕ ነህ” የሚለውን፣ሕዝቦች ይረግሙታል፤ መንግሥታትም ያወግዙታል።

25 በደለኛውን፣ “አንተ ጥፋተኛ ነህ” የሚሉት ግን መልካም ነገር ይገጥማቸዋል፤የተትረፈረፈ በረከትም ይወርድላቸዋል።

26 እውነተኛ መልስ መስጠት፣ከንፈርን እንደ መሳም ነው።

27 በደጅ ያለውን ሥራህን ፈጽም፤ዕርሻህን አዘጋጅ፤ከዚያም በኋላ ቤትህን ሥራ።

28 በባልንጀራህ ላይ ያለ ምክንያት አትመስክር፤በከንፈርህም አትሸንግል።

29 “በእኔ ላይ እንደ ሠራብኝ እሠራለታለሁ፤ስለ አድራጎቱም የጁን እመልስለታለሁ” አትበል።

30 በሰነፍ ሰው ዕርሻ በኩል አለፍሁ፤ማስተዋል የጐደለውን ሰው የወይን ቦታ አልፌ ሄድሁ፤

31 በያለበት እሾህ በቅሎበታል፤መሬቱም ዐረም ለብሶአል፤ቅጥሩም ፈራርሷል።

32 ያየሁትን ነገር አወጣሁ አወረድሁ፤ካስተዋልሁትም ትምህርት አገኘሁ፤

33 “ጥቂት ላንቀላፋ፣ ጥቂት ላሸልብ፣እጄን አጣጥፌ ጥቂት ልረፍ” ብትል፣

34 ድኽነት እንደ ወንበዴ፣እጦትም እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31