1 ልጄ ሆይ፤ ለጎረቤትህ ዋስ ብትሆን፣ስለ ሌላውም ሰው እጅ መትተህ ቃል ብትገባ፣
2 በተናገርኸው ነገር ብትጠመድ፣ከአፍህ በወጣውም ቃል ብትያዝ፣
3 ልጄ ሆይ፤ ራስህን ለማዳን ይህን አድርግ፤በጎረቤትህ እጅ ስለ ወደቅህ፣ሄደህ ራስህን አዋርድ፤ጎረቤትህን አጥብቀህ ነዝንዘው።
4 ዐይኖችህ እንቅልፍ አይያዛቸው፣ሽፋሽፍቶችህም አያንጐላጁ።
5 ከአዳኝ እጅ እንዳመለጠች ሚዳቋ፣ከአጥማጅ ወጥመድ እንዳፈተለከች ወፍ ራስህን አድን።
6 አንተ ታካች፤ ወደ ጒንዳን ሂድ፤ዘዴውን አስተውለህ ጠቢብ ሁን፤
7 አዛዥ የለውም፤አለቃም ሆነ ገዥ የለውም፤
8 ሆኖም ግን በበጋ ምግቡን ያከማቻል፤በመከርም ወቅት ቀለቡን ይሰበስባል።
9 አንተ ታካች፤ እስከ መቼ ትተኛለህ?ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ?
10 ጥቂት ማንቀላፋት፤ ጥቂት ማንጐላቸት፤እጅን አጣጥፎ “እስቲ ጥቂት ልረፍ” ማለት፤
11 ድኽነት እንደ ወንበዴ፣ዕጦትም መሣሪያ እንደ ታጠቀ ሰው ከተፍ ይልብሃል።
12 ወሮበላና ጨካኝ፣ነውረኛ አንደበቱን ይዞ የሚዞር፣
13 በዐይኑ የሚጠቅስ፣በእግሩ ምልክት የሚሰጥ፣በጣቶቹ የሚጠቊም፣
14 በልቡ ተንኰል ክፋትን የሚያውጠነጥን፣ምንጊዜም ጠብ ይጭራል።
15 ስለዚህ በቅጽበት መዓት ይወርድበታል፤በድንገት ይጠፋል፤ መዳኛም የለውም።
16 እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች አሉ፤የሚጸየፋቸውም ሰባት ናቸው፤ እነርሱም፦
17 ትዕቢተኛ ዐይን፣ሐሰተኛ ምላስ፣ንጹሕ ደም የሚያፈሱ እጆች፣
18 ክፋትን የሚያውጠነጥን ልብ፣ወደ ክፋት የሚቻኰሉ እግሮች፣
19 በውሸት ላይ ውሸት የሚጨምር ሐሰተኛ ምስክር፣በወንድማማቾች መካከል ጠብን የሚጭር ሰው።
20 ልጄ ሆይ፤ የአባትህን ትእዛዝ አክብር፤የእናትህንም ትምህርት አትተው።
21 ምንጊዜም በልብህ አኑራቸው፤በዐንገትህም ዙሪያ እሰራቸው።
22 በምትሄድበት ሁሉ ይመሩሃል፤በምትተኛበት ጊዜ ይጠብቁሃል፤በምትነቃበት ጊዜም ያነጋግሩሃል።
23 እነዚህ ትእዛዞች መብራት ናቸውና፤ይህችም ትምህርት ብርሃን፣የተግሣጽ ዕርምትም የሕይወት መንገድ ናት፤
24 እርሷም ከምግባረ ብልሹ ሴት፣ልዝብ አንደበት ካላት ዘልዛላ ሴት ትጠብቅሃለች።
25 ውበቷን በልብህ አትመኝ፤በዐይኗም አትጠመድ፤
26 ጋለሞታ ሴት ቊራሽ እንጀራ ታሳጣሃለችና፤አመንዝራዪቱም በሕይወትህ በራሱ ላይ ትሸምቃለች።
27 ለመሆኑ ልብሱ ሳይቃጠል፣በጒያው እሳት መያዝ የሚችል ሰው አለን?
28 አንድ ሰው እግሮቹ ሳይቃጠሉ፣በፍም ላይ መሄድ ይችላልን?
29 ከሰው ሚስት ጋር የሚተኛም እንደዚሁ ነው፤የሚደርስባትም ከቅጣት አያመልጥም።
30 ሌባ በተራበ ጊዜ ራቡን ለማስታገሥ ቢሰርቅ፣ሰዎች አይንቁትም።
31 በቤቱ ያለውን ሀብት ሁሉ የሚጠይቀው ቢሆንም፣ከተያዘ ሰባት ዕጥፍ መክፈል አለበት።
32 የሚያመነዝር ሰው ግን ማመዛዘን ይጐድለዋል፤እንዲህ የሚያደርግ ሁሉ ራሱን ያጠፋል።
33 መደብደብና ውርደት ዕጣው ነው፤ኀፍረቱም ከቶ አይወገድም፤
34 ቅናት የባልን ቊጣ ይቀሰቅሳልና፤በሚበቀልበትም ጊዜ ምሕረት አያደርግም።
35 ምንም ዐይነት ካሣ አይቀበልም፤የቱንም ያህል ብዙ ቢሆን መማለጃን እሺ አይልም።