ምሳሌ 19 NASV

1 ንግግሩ ጠማማ ከሆነ ዐጒል ሰው ይልቅ፣ያለ ነውር የሚሄድ ድኻ ሰው ይሻላል።

2 ዕውቀት አልባ የሆነ ቀናዒነት መልካም አይደለም፤ጥድፊያም መንገድን ያስታል።

3 ሰው በራሱ ተላላነት ሕይወቱን ያበላሻል፤በልቡ ግን እግዚአብሔርን ያማርራል።

4 ሀብት ብዙ ወዳጅ ታፈራለች፤ድኻን ግን ወዳጁ ገሸሽ ያደርገዋል።

5 ሐሰተኛ ምስክር ከቅጣት አያመልጥም፤ውሸት የሚነዛም ሳይቀጣ አይቀርም።

6 ብዙ ሰዎች በገዥ ዘንድ ሞገስ ለማግኘት ያሸረግዳሉ፤ስጦታን ከሚሰጥ ሰው ጋር ሁሉም ወዳጅ ነው።

7 ድኻ በሥጋ ዘመዶቹ ሁሉ የተጠላ ነው፤ታዲያ ወዳጆቹማ የቱን ያህል ይሸሹት!እየተከታተለ ቢለማመጣቸውም፣ከቶ አያገኛቸውም።

8 ጥበብን ገንዘቡ የሚያደርጋት ነፍሱን ይወዳል፤ማስተዋልን የሚወዳት ይሳካለታል።

9 ሐሰተኛ ምስክር ከቅጣት አያመልጥም፤ውሸት የሚነዛም ይጠፋል።

10 ተላላ ተንደላቆ መኖር አይገባውም፤ባሪያ የመሳፍንት ገዥ ከሆነማ የቱን ያህል ይከፋ!

11 ጥበብ ሰውን ታጋሽ ታደርገዋለች፤በደልን ንቆ መተውም መከበሪያው ነው።

12 የንጉሥ ቊጣ እንደ አንበሳ ግሣት ነው፤በፊቱ ሞገስ ማግኘትም በሣር ላይ እንዳለ ጠል ነው።

13 ተላላ ልጅ ለአባቱ መጥፊያ ነው፤ጨቅጫቃ ሚስትም እንደማያቋርጥ ጠፈጠፍ ናት።

14 ቤትና ሀብት ከወላጆች ይወረሳሉ፤አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት።

15 ስንፍና ከባድ እንቅልፍ ላይ ይጥላል፤ዋልጌም ሰው ይራባል።

16 ትእዛዛትን የሚያከብር ሕይወቱን ይጠብቃል፤መንገዱን የሚንቅ ግን ይሞታል።

17 ለድኻ የሚራራ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ስላደረገውም ተግባር ዋጋ ይከፍለዋል።

18 ገና ተስፋ ሳለ፣ ልጅህን ሥርዐት አስይዘው፤ሲሞት ዝም ብለህ አትየው።

19 ግልፍተኛ ሰው ቅጣትን መቀበል ይገባዋል፤በምሕረት ካለፍኸው ሌላም ጊዜ አይቀርልህም።

20 ምክርን ስማ፤ ተግሣጽን ተቀበል፤በመጨረሻም ጠቢብ ትሆናለህ።

21 በሰው ልብ ብዙ ሐሳብ አለ፤የሚፈጸመው ግን የእግዚአብሔር ሐሳብ ነው።

22 ሰው የሚመኘው ጽኑ ፍቅር ነው፤ውሸታም ከመሆንም ድኻ መሆን ይሻላል።

23 እግዚአብሔርን መፍራት ወደ ሕይወት ይመራል፤እንዲህ ያለውም ሰው እፎይ ብሎ ያርፋል፤ መከራም አያገኘውም።

24 ሰነፍ እጁን ከወጭቱ ያጠልቃል፤ወደ አፉ ግን መመለስ እንኳ ይሳነዋል።

25 ፌዘኛን ግረፈው፤ ብስለት የሌለውም ማስተዋልን ይማራል፤አስተዋይን ዝለፈው፤ ዕውቀትን ይገበያል።

26 አባቱን የሚዘርፍ፣ እናቱንም የሚያሳድድ፣ዕፍረትና ውርደት የሚያመጣ ልጅ ነው።

27 ልጄ ሆይ፤ እስቲ፣ ምክርን ማዳመጥ ተው፤ከዕውቀትም ቃል ትስታለህ።

28 ዐባይ ምስክር በፍትሕ ላይ ያፌዛል፤የክፉዎችም አፍ በደልን ይሰለቅጣል።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31