ምሳሌ 15 NASV

1 የለዘበ መልስ ቊጣን ያበርዳል፤ክፉ ቃል ግን ቊጣን ይጭራል።

2 የጠቢብ አንደበት ዕውቀትን ታወድሳለች፤የተላሎች አንደበት ግን ቂልነትን ያፈልቃል።

3 የእግዚአብሔር ዐይኖች በሁሉም ስፍራ ናቸው፤ክፉዎችንም ደጎችንም ነቅተው ይመለከታሉ።

4 ፈውስ የምታመጣ ምላስ የሕይወት ዛፍ ናት፤አታላይ ምላስ ግን መንፈስን ትሰብራለች።

5 ተላላ የአባቱን ምክር ይንቃል፤መታረምን የሚቀበል ግን አስተዋይነቱን ያሳያል።

6 የጻድቃን ቤት በብዙ ሀብት የተሞላ ነው፤የክፉዎች ገቢ ግን መከራን ታመጣባቸዋለች።

7 የጠቢባን ከንፈር ዕውቀትን ታስፋፋለች፤የተላሎች ልብ ግን እንዲህ አይደለም።

8 እግዚአብሔር የክፉዎችን መሥዋዕት ይጸየፋል፤የቅኖች ጸሎት ግን ደስ ያሰኘዋል።

9 እግዚአብሔር የክፉዎችን መንገድ ይጸየፋል፤ጽድቅን የሚከታተሉትን ግን ይወዳቸዋል።

10 ከመንገድ የሚወጣ ሰው ጥብቅ ቅጣት ይጠብቀዋል፤ዕርምትን የሚጠላ ይሞታል።

11 ሲኦልና የሙታን ዓለም በእግዚአብሔር ፊት የተገለጡ ናቸው፤የሰዎች ልብ ማየቱን ያህል የታወቀ ነው!

12 ፌዘኛ መታረምን ይጠላል፤ጠቢባንንም አያማክርም።

13 ደስተኛ ልብ ፊትን ያፈካል፤የልብ ሐዘን ግን መንፈስን ይሰብራል።

14 አስተዋይ ልብ ዕውቀትን ይሻል፤የተላላ አፍ ግን ቂልነትን ያመነዥካል።

15 የተጨቈኑ ሰዎች ዘመናቸው ሁሉ የከፋ ነው፤በደስታ የተሞላ ልብ ግን የማይቋረጥ ፈንጠዝያ አለው።

16 እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር፣ሁከት ካለበት ትልቅ ሀብት ይበልጣል።

17 ፍቅር ባለበት ጐመን መብላት፣ጥላቻ ባለበት የሰባ ፍሪዳ ከመብላት ይሻላል።

18 ግልፍተኛ ሰው ጠብ ያነሣሣል፤ታጋሽ ሰው ግን ጠብን ያበርዳል።

19 የሀኬተኛ መንገድ በእሾህ የታጠረች ናት፤የቅኖች መንገድ ግን የተጠረገ አውራ ጐዳና ነው።

20 ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ተላላ ሰው ግን እናቱን ይንቃል።

21 ማመዛዘን የጐደለው ሰው ቂልነት ያስደስተዋል፤አስተዋይ ሰው ግን ቀጥተኛውን መንገድ ይከተላል።

22 ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል፤በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል።

23 ሰው ተገቢ መልስ በመስጠት ደስታን ያገኛል፤በወቅቱም የተሰጠ ቃል ምንኛ መልካም ነው!

24 ወደ ሲኦል ከመውረድ እንዲድን፣የሕይወት መንገድ ጠቢቡን ሰው ወደ ላይ ትመራዋለች።

25 እግዚአብሔር የትዕቢተኛውን ቤት ያፈርሰዋል፤የመበለቲቱን ዳር ድንበር ግን እንዳይደፈር ይጠብቃል።

26 እግዚአብሔር የክፉውን ሰው ሐሳብ ይጸየፋል፤የንጹሓን ሐሳብ ግን ደስ ያሰኘዋል።

27 ስስታም ሰው በቤተ ሰቡ ላይ ችግር ያመጣል፤ጒቦን የሚጠላ ግን በሕይወት ይኖራል።

28 የጻድቅ ሰው ልብ የሚሰጠውን መልስ ያመዛዝናል፤የክፉ ሰው አፍ ግን ክፋትን ያጐርፋል።

29 እግዚአብሔር ከክፉዎች ሩቅ ነው፤የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል።

30 ብሩህ ገጽታ ልብን ደስ ያሰኛል፤መልካም ዜናም ዐጥንትን ያለመልማል።

31 ሕይወት ሰጪ የሆነውን ተግሣጽ የሚሰማ፣በጠቢባን መካከል ይኖራል።

32 ተግሣጽን የሚንቅ ራሱን ይንቃል፤ዕርምትን የሚቀበል ግን ማስተዋልን ያገኛል።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31